ሀዋሳ ከተማ ከአምስት ጨዋታ ድል አልባ ጉዞ በኋላ ወላይታ ድቻን 2ለ1 በመርታት ከድል ጋር ታርቀዋል።
ቡድኖቹ ካለፈው ሳምንት ጨዋታቸው አኳያ ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከረታበት ስብስቡ ጉዳት በገጠመው አብነት ደምሴን በመሳይ ኒኮል ፣ ፍፁም ግርማን በእዮብ ተስፋዬ ሲቀይሩ በመቻል ሽንፈት አስተናግደው በነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በኩል በተደረገ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በረከት ሳሙኤል ፣ ሚሊየን ሠለሞን ፣ አቤኔዘር ዮሐንስ እና ማይክል ኦቱሉ አርፈው ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ መድሀኔ ብርሀኔ ፣ ዳዊት ታደሠ እና እዮብ አለማየሁ ተተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ቀዳሚ ጨዋታ ጎልን ያስመለከተን ገና በ3ኛው ደቂቃ ላዬ ነበር። ኳሱን ከመሐል ሜዳ ያስጀመሩት እና በንክኪ የወላይታ ድቻ የግብ ክልል የደረሱት ሀዋሳ ከተማዎች ዓሊ ከቀኝ ወደ ውስጥ የሰጠውን ኳስ እዮብ ዓለማየሁ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሲመታው ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መቆጣጠር የተሳነውን ኳስ ተባረክ ሄፋሞ መረቡ ላይ አሳርፎ ሀይቆቹን መሪ አድርጓል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ በይበልጥ የመሐል ክፍሉን ከሁለቱ ኮሪደሮች ጋር በማስተሳሰር ወደ ጨዋታ ለመመለስ የጣሩት ወላይታ ድቻዎች 7ኛው ደቂቃ ከቀኝ ወደ ውስጥ ተሻምቶ እንየው ለግብ ጠባቂው ሉክዋንጎ ለማቀበል ያሳጠረውን ኳስ ቢኒያም ፍቅሬ ደርሶ ሳይጠቀምባት ቀርቷል።
ያልተረጋጉ የኳስ ቅብብሎችን እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች ኳስን በመያዝ በድግግሞሽ ሳይቸገሩ የሀዋሳ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም በቀላሉ ያገኟቸውን የነበሩትን ዕድሎች ከመጠቀሙ አንፃር ስኬታማ አልነበሩም። 16ኛው ደቂቃ ድቻዎች ቢኒያም ከማዕዘን ምት አሻምቶ ፀጋዬ በግንባር ጨርፎ ያቀበለውን ኳስ አበባየሁ ሀጂሶ መረቡ ላይ አሳረፈው ተብሎ ሲጠበቅ ቻርለስ ሉክዋንጎ መልሶበታል። ጨዋታውን ይቆጣጠሩ እንጂ የሀዋሳን የመልሶ ማጥቃት መቋቋም ያቃተው የወላይታ ድቻ የኋላ መስመር በፀጋዬ ብርሀኑ የግንባር ሙከራን ካደረጉ ከሁለት ደቂቃዎች መልስ ጎል ተቆጥሮባቸዋል።
26ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ናትናኤል ናሲሩ ኳስን ወደ ኋላ ማቀበል የቻለውን ኳስ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መቆጣጠር ተስኖት ከእግሩ ስር እዮብ አለማየሁ ነጥቆት የቀድሞው ክለቡ ላይ በማስቆጠር የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሁለት አሳድጓል። ኳስን በተሻለ ማንሸራሸር ቢችሉም በሀዋሳ የመልሶ ማጥቃት በእጅጉ የተፈተኑት ድቻዎች ተጨማሪ ግቦችን ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። 45+3 ላይ ዳዊት በረጅሙ የሰጠውን ዓሊ ሱለይማን አረጋግቶ ወደ ግብ ተፈጥሯዊ ባልሆነው እግሩ መቶ ቢኒያም የመለሰበት እና ከአንድ ደቂቃ መልስ ተባረክ ሄፋሞ ከማዕዘን የደረሰውን ኳስ ሁለት ጊዜ ሞክሮ ቢኒያም ከመለሰበት በኋላ አጋማሹ በሀዋሳ 2ለ0 ተጋምሷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ መጠነኛ ፉክክርን ያየንበት እንጂ ከሙከራዎች አንፃር መቀዛቀዝን በይበልጥ ያስተዋልንበት ነበር ማለት ይቻላል። ሁለት ጎሎችን በማስቆጠራቸው ጥንቃቄ ላይ በአመዛኙ በማጋደል በሽግግር ለመጫወት ዓሊ ሱለይማንን ሀዋሳዎች ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው ከጎል ጋር ለመገናኘት ከማንኛውም የሜዳ ክፍል በሰንጣቂ እና ተንጠልጣይ ኳሶች ግቦች ለማስቆጠር በብርቱ ቢታገሉም የሀዋሳን የመከላከል አደረጃጀት ለመስመር አልቻሉም።
ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ ፀጋዬ ብርሀኑ እና ዘላለም አባተን በዮናታን ኤልያስ እና ብስራት በቀለ የተኩት ወላይታ ድቻዎች ከለውጡ በኋላ ከተጋጣሚያቸው ሻል ባለ መልኩ ቢንቀሳቀሱም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚያገኟቸውን ኳሶች ያመክኗቸው ነበር ፣ ይሁን እንጂ ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ መነቃቃታቸው በደንብ እያጎለበቱ የቀጠሉት የጦና ንቦቹ 70ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝተዋል። በተንጠልጣይ ኳስ ተከላካዩ ፀጋአብ ዮሐንስ በግንባር ገጭቶ ለማውጣት ሲዳዳ ከፊቱ የነበረው ተቀይሮ የገባው ዮናታን ኤልያስ ሉክዋንጎ መረብ ላይ ኳሷን አስቀምጧት ጨዋታው ወደ 2ለ1 ተሸጋግሯል።
ከጎሏ መቆጠር በኋላ ድቻ በኬኔዲ ከበደ ጥሩ አጋጣሚን ቢያገኙም በቀላለ ግብ ጠባቂውን አሳቅፎታል። ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ሀዋሳ በዓሊ እና ተቀይሮ በገባው በምንተስኖት እንድሪያስ ያለቀለትን ሙከራ ቢያደርጉም ጨዋታው በመጨረሻም በሀይቆቹ የ2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።