መረጃዎች| 45ኛ የጨዋታ ቀን

የአስራ አንደኛው ሣምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገ ይገባደዳሉ። የሣምንቱን ትልቅ ጨዋታ ጨምሮ እስካሁን ድረስ ድል ማስመዝገብ ያልቻሉ ሁለት ቡድኖችን የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።


ሀምበርቾ ከ ሻሸመኔ ከተማ

የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በውድድር ዓመቱ ድል ያላደረጉ ሁለት ክለቦችን ያገናኛል።

በአስረኛው የጨዋታ ሣምንት ከአምስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ከጠንካራው ባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት ሀምበርቾዎች በሦስት ነጥቦች የሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛሉ። ሀምበርቾዎች የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ የአጨዋወት ለውጥ አድርገው ጠጣርና የሚከላከል ቡድን ገንብተዋል። ይህ አጨዋወትም ከንግድ ባንክና ባህርዳር ከተማ ጋር ባደረጓቸው ሁለተ ጨዋታዎች ተስተውሏል። በተለይም ከጣና ሞገዶቹ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ለተጋጣሚ ፈታኝ የሆነና ጥቅጥቅ ብሎ የሚከላከል አደረጃጀት ይዘው ገብተው አንድ ነጥብ አሳክተዋል። በጨዋታው 35ኛ ደቂቃ ላይ ብሩክ ቃልቦሬ በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክንያት በጎዶሎ ለመጫወት ተገደው ከጠንካራው ተጋጣሚ አንድ ነጥብ መውሰዳቸውም ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ምን ያህል እንደተሻሻለ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ብሩክ ሲሣይ የቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት ላይ ለውጥ ቢያመጡም ላለፉት ሰባት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ያላገናኘውን ደካማውን የፊት መስመር ማስተካከል ቀላል አልሆነላቸውም። በነገው ጨዋታም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱን ውጤታማነት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች አስመዝግበው ነጥባቸውን ወደ አራት ያደረሱት ሻሸመኔ ከተማዎች እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ አጨዋወታቸውን ከቀየሩ ሰንበትበት ብለዋል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎችም በአመዛኙ መከላከል ላይ የተመሰረተና በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ከቡድኑ መንፈስ በተጨማሪ በአጨዋወቱ ላይም በጎ ለውጦች ማምጣት የቻሉት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በቀጣይ ቡድኑ ከመከላከል በዘለለ ስል የፊት መስመር እንዲኖረው የሚያደርግ ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋል። በእርግጥ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጉት የመጨረሻው ሣምንት ጨዋታ ላይ በመልሶ ማጥቃትና በቀጥተኛ አጨዋወት ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም አሁንም መሻሻል የሚፈልግ የፊት መስመር ነው ያላቸው።

ሀምበርቾዎች በነገው ጨዋታ የበፍቃዱ አስረሳኸኝ እና ቴዎድሮስ በቀለን ግልጋሎት አያገኙም። በሻሸመኔ ከተማ በኩልም ቻላቸው መንበሩ በጉዳት ምክንያት አይኖርም ፣ የባለፈው ጨዋታ ላይ በቅጣት ምክንያት ያልተሰለፈው ጋናዊ አማካይ ማይክል ኔልሰን ግን ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሠ ረዳቶች አለማየሁ ታደሠ በአንፃሩ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል።


ፋሲል ከነማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ዐፄዎቹን እና ፈረሠኞቹን የሚያገናኘው የሣምንቱ ትልቅ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

ከተከታታይ ሽንፈት አገግመው ሁለት ተከታታይ ድል ያስመዘገቡት ዐፄዎቹ ይህንን ወሳኝ ጨዋታ ካሸነፉ ነጥባቸውን ወደ ሀያ አንድ አድርሰው ሁለት ደረጃዎች የሚያሻሽሉበት ዕድል በእጃቸው ላይ አለ። ዐፄዎቹ በጌታነህ ከበደ ግሩም የቅጣት ምት ግብ ታግዘው ወልቂጤ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ከወትሮ የደከመ የአማካይ ክፍል ነበራቸው። ይህንን ተከትሎም ከዛ በፊት ባደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ እንደነበራቸው ጨዋታን የመቆጣጠር ብልጫ ማስመዝገብ አልቻሉም። በነገው ጨዋታም በሁለት የአማካይ ተከላካይ ለመጫወት የሚሞክርና ጠጣር የአማካይ ክፍል ያለው ቡድን ስለሚገጥሙ ባለፈው ጨዋታ የታዩባቸው ክፍተቶች መድፈን ይጠበቅባቸዋል። ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መመለሱን ተከትሎ በፊት መስመር የነበረባቸው ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ውስንነት የፈቱት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመከላከሉ ረገድም ለተጋጣሚ ፈታኝ የሆነ የኋላ ክፍል ገንብተዋል። ቡድኑም ሰባት ግቦች ብቻ በማስተናገድ ቀዳሚ ከሆኑት ከሀዲያ ሆሳዕና እና ንግድ ባንክ በመቀጠል ከሲዳማ ቡና ዕኩል ሁለተኛውን ዝቅተኛ የግብ መጠን (8) ያስተናገደ የተከላካይ ክፍል አለው። በነገው ዕለትም በሊጉ ከፍተኛውን የግብ መጠን ያስቆጠረ የፈረሠኞቹ የፊት መስመርና ጠጣሩ የዐፄዎቹ የኋላ ክፍል የሚያደርጉት ፍጥጫ ትኩረትን ይስባል።

ሊጉ ከዕረፍት ከተመለሰ በኋላ የቀደመ ብቃታቸውን ለማግኘት የተቸገሩት ፈረሠኞቹ ከተጠቀሰው ወቅት በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ድል፣ ሁለት አቻ እና አንድ ሽንፈት አስተናግደዋል። ውጤቱ እንደሚያመላክተው ፈረሠኞቹ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ አይገኙም። በነገው ዕለትም ከሦስት ድል አልባ ጨዋታዎች መልስ ዳግም ሙሉ ሦስት ነጥብ አግኝተው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። ፈረሠኞቹ በሊጉ አስፈሪ የሚባል የማጥቃት ጥምረት ካላቸው ቡድኖች ይጠቀሳሉ። ቡድኑ ያስቆጠረው የግብ መጠንም የዚህ ምስክር ነው። ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ግን ስል የሆነ የፊት መስመር ነበራቸው ብሎ መናገር አይቻልም። ከዚ ቀደም በመስመሮች በሚደረግ ፈጣን ሽግግር የግብ ዕድሎች የሚፈጥር ቡድን ያስመለከቱን አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የተቀዛቀዘውን የፊት መስመር ዳግም ወደ ጥንካሬው የሚመልስ ውስን ጥገና ማድረግ ይኖርባቸዋል። በመጨረሻው ጨዋታ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለውን ሀዲያን ገጥመው ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በነገው ዕለትም ተመሳሳይ ፈተና ሊገጥማቸው የሚችልበት ዕድል የሰፋ ስለሆነ አሰልጣኙ ለውጦችን ለማድረግ ይገደዳሉ ተብሎም ይገመታል።

ፈረሠኞቹ በቅጣት የሰነበተውን ሞሰስ ኦዶን ዳግም አግኝተዋል። ሌላው በጉዳት ላይ የነበረው በረከት ወልዴ ከጉዳት ቢያገግምም ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው። የፋሲል ከነማን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ስልካቸውን ለማንሳት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ልናካትተው አልቻልንም።

የሳምንቱን የመጨረሻ ጨዋታን ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ ረዳቶቹ ሌላኛው ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።