አፍሪካ ዋንጫ | ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ግልጋሎት ይሰጣሉ

በአፍሪካ ዋንጫው የሀገራችን ብቸኛ የቴክኒክ ጥናት ቡድን ውስጥ የተካተቱት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ዛሬ የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሙያዊ ግልጋሎት እንዲሰጡ ተመድበዋል።

በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው አይቮሪኮስት እየተከናወነ የሚገኘው የአህጉሪቱ ትልቁ የውድድር መድረክ የአፍሪካ ዋንጫ ከተጀመረ ዛሬ 7ኛ ቀኑን መያዙ ይታወቃል። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያን በሦስት ሙያዎች የወከሉት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣ አልቢትር ባምላክ ተሰማ እና ኮሚሽነር ተስፋነሽ ወረታ ያለፉትን ቀናት ግልጋሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የቴክኒክ ጥናት ቡድን አባል ሆነው ያገለገሉት የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር እና የፊፋ ቴክኒካል ኤክስፐርት አብርሃም መብራቱ ዘንድሮም የአፍሪካ ዋንጫው ቴክኒካል ጥናት ቡድን አባል ከሆኑ 19 ግለሰቦች መካከል አንዱ መሆናቸው ይታወቃል። ከቀድሞ ታላላቅ ተጫዋቾች እና ባለሙያዎች ጋር በቴክኒካል ጥናት ቡድኑ ውስጥ የሚገኙት ኢንስትራክተር አብርሃም የምድብ 4 ጨዋታዎችን እየገመገሙ የሚገኝ ሲሆን ባለፉት ቀናትም አልጄሪያ ከአንጎላ እንዲሁም ቡርኪናፋሶ ከሞሪታኒያ ያደረጉት ጨዋታ ላይ ተመድበው ግልጋሎት ሰጥተዋል።

ኢንስትራክተር አብርሃም ዛሬ ደግሞ የምድቡ ተጠባቂ ጨዋታ የሆኑትን የአልጄሪያ እና ቡርኪናፋሶ እንዲሁም ሞሪታኒያ እና አንጎላ ጨዋታዎች እንዲያጠኑ ከኬኒያዊው አቻቸው ሚኬል አሜንጋ ጋር በመሆን መመደባቸው ታውቋል።

*ድረ-ገፃችን ከውድድሩ ስፋራ ባገኘችው መረጃ 11 ሰዓት የሚደረገውን የአልጄሪያ እና ቡርኪናፋሶ ጨዋታ ባምላክ ተሰማ በአራተኛ ዳኝነት ይመራዋል ብላ ከሰዓታት በፊት መረጃ ብታጋራም የዳኞች ለውጥ መደረጉንና ጨዋታውን በአራተኛ ዳኝነት ብሩንዲያዊው ንዳቢሃወኒማና ፓስፊክ እንደሚመሩት አውቀናል።