ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ‘ለ’ የአንደኛው ዙር የመጨረሻ ሳምንት በሁለተኛ ቀን አራት ጨዋታዎች ተደርገው ቦዲቲ ከተማ እና ደብረብርሃን ከተማ የዕለቱ ባለድል ሆነዋል።

ረፋድ 3 ሰዓት ሲል በተጀመረው መርሃ ግብር ባቱ ከተማ ከ የካ ክፍለከተማ ተገናኝተው ነጥብ ተጋርተዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ብዙም የግብ ሙከራ አላስመለከቱም ነበር። ሆኖም ግን ባቱ ከተማዎች ከተጋጠሚያቸው ብልጫ መውሰድ ችለዋል። ባቱዎቹ አልፈው አልፈው በሚያድርጉት በአንድ ለአንድ ቅብብል ብዙ ለግብ የተቃረቡ ኳሶችን መፍጠር ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል።


የካዎች በአንፃሩ እምብዛም የግብ ሙከራ ሳያድርጉ ደካማ የጨዋታ እንቅስቃሴ ያሳዩበትን አርባአምስት አሳልፈዋል። እንዲሁም በኳስ ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ በተጋጣሚዎቻቸው ተወስዶባቸዋል። ሆኖም ግን በ34ኛው ደቂቃ ያገኙትን እድል በመጠቀም ረጀ ነጋሽ በእራሱ ጥረት ኳስና መረብ አገናኝቶ መሪ መሆን ችለዋል።

ቢሆንም በመሪነት መቆየት የቻሉት ለ2 ደቂቃ ብቻ ነበር። የጨዋታ ብልጫ የወሰዱትን አጋጣሚ የተጠቀሙት ባቱዎች በ36ኛው ደቂቃ እስራኤል ሸጎሌ በእርስ በእርስ ቅበብል የተገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ አንድ እኩል እንዲሆኑ አስችለዋል።

በአንድ ግብ ብቻ አላበቃ ያሉት ባቱዎቹ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲጣጣሩ ተስተውለዋል። የአንደኛው አጋማሽ በዚሁ ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃ ላይ የባቱ ከተማው አምበል ሀቢብ ጀለቶ ራቅ ካለ ቦታ መትቶ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ 2ለ1 እየመሩ እረፍት እንዲወጡ አድርጓል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመመለስ በጫና ወደ ሜዳ የተመለሱት የካዎቹ የአቻነት ግብ ፍለጋ በርከት ያለ የግብ ሙከራ አድርገዋል። እንዲሁም የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ወደጨዋታ መመለስ ችለዋል። ከብዙ ግብ ሙከራ በኋላ በ71ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስ አግንተው ተቀይሮ የገባው ጌታሁን አየለ ቀጥታ ወደግብ መጥቶ አስቆጥሮ 2ለ2 እኩል እንዲሆኑ አድርጓል። አቻ ከሆኑ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል ሆኖም ግን ሌላ ግብ አላስመለከቱም። ጨዋታውም 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በማስከተል የተደረገው ጨዋታ ደብረብርሃን ከተማን ከኦሜድላ አገናኝቷል። ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በመልሶ ማጥቃት ግቦችን ለማስቆጠር ሙከራ ሲያድርጉ ተስተውለዋል። የመጀመሪያዎቹን 25 ደቂቃዎች ጥሩ የነበሩት ኦሜድላዎች ብዙ ለግብ የተቃረቡ ኳሶችን አግኝተው መጠቀም አልቻሉም። በ23ኛው ደቂቃ ሰይፈ ዛኪር ከመሃል ሜዳ አከባቢ ያገኘውን ኳስ የደብረብርሃን ከተማ ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂውን አታሎ በማለፍ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ መሪ አድርጓቸዋል።

ብርሃኖቹ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ የኳስ ፍሰቱን ወደፊት አድርገው ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲገቡ ተስተውለዋል። በ28ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም መሀመድ ከግብ ክልል ራቅ ብሎ የመታት ኳስ የግብ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ይታወሳል። በ38ኛው ደቂቃ አብዱልመጅድ ሁሴን በራሱ ጥረት ያገኛችን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቶእረፍት ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ አስችሏል።

 

በሁለተኛ አጋማሽ ተሽለው የተመለሱት ደብረብርሃን በኳስ ቁጥጥር ተቃራኒ ቡድንን በልጦ መታየት ችለዋል። እንዲሁም ብዙ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። በኦሜድላ ተከላካዮች በሚሰሩ ጥፋቶች የቆሙ ኳሶችን አግኝተው ወደግብ ለመቀየር የሞከሩት አጋጣሚዎች ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ በታየው ውስጥ የኦሜድላ ተከላካዮች አደገኛ ቦታ ላይ ጥፋት ፈፅመው ቅጣት ምት ለብርሃኖቹ ተሰጥቷቸው ተቀይሮ የገባው አምበላቸው ቢያድግልኝ ኤልያስ 90+3 ላይ ቅጣት ምቷን ወደግብነት ቀይረው ብርሃኖቹ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በድል እንዲጨርሱ አድርጓል።

የእለቱ ሦስተኛ ጨዋታ ቦዲቲ ከተማን ከወሎ ኮምቦልቻ አገናኝቷል። ጥሩ የጨዋታ ፉክክር የታየበት የስምንት ሰዓቱ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በቦዲቲ ከተማ በላይነት ተጠናቋል። የግብ ሙከራ ገና ጨዋታ እንደጀመረ የጀመሩት ቦዲቲ ከተማዎች ከማራኪ ከኳስ ቁጥጥር ጋር የታጀበ እንቅስቃሴ በማሳየት ለግብ የተቃረቡ ኳሶችን ወደተቃራኒ ቡድን ይዞ መግባት ችለዋል። በ8ኛው ደቂቃ የመስመር አጥቂ ተጫዋች የሆነው ሙሉቀን ተስፋዬ በመስመር በኩል የወሎ ኮምቦልቻን ተከላካዮች አታሎ በማለፍ ኳሱን ይዞ ገብቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ቦዲቲ ከተማን መሪ አድርጓል።

ወሎ ኮምቦልቻዎች በአንፃሩ ደካማ የሚባል የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፉ ሲሆን ግብ ቢቆጠርባቸውም የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሲያድርጉ አልተስተዋሉም። ይልቁንስ ተጋጣሚያቸው ቦዲቲ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያድርግ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን በአንደኛው አጋማሽ ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ወደመልበሻ ክፍል ተመልሰዋል።

ቦዲቲ ከተማዎች ከአንደኛው አጋማሽ አንፃር በሁለተኛው አጋማሽ  ትንሽ ተዳክመው የተመለሱበትን አጋማሽ አስመልክተዋል። ሆኖም ግን መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ እስኪቀር ድረስ ግባቸውን ሳያስደፍሩ መቆየት ችለዋል። ወሎ ኮምቦልቻዎች በአንፃሩ የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩበትን ሁለተኛ አጋማሽ ማሳለፍ የቻሉ ሲሆን የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስመለስ ጥረት አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ቦዲቲ ከተማዎችም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድፈር ጥረት አድርገዋል። በተለያዩ አጋጣሚ የተፈጠሩ ለግብ የተቃረቡ ኳሶችን ሁለቱም ቡድኖች ሳይጠቀሙ መቅረታቸው የሚታወስ ነው። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃ ሲቀረው በ85ኛው ደቂቃ የወሎ ኮምቦልቻው ተጫዋች የሆነው ማኑሄ ጌታቸው በአንድ ለአንድ ቅበብል የተገኘውን ኳስ እንዴትም ብሎ አስቆጥሮ አቻ በማድረግ ወሎ ኮምቦልቻዎችን ወደ ጨዋታ እንዲመለሱ ማድረግ ችሏል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ የዕለቱ ዋና ዳኛ ጭማሪ ባሳዩት ላይ የመጨረሻ እድል የሆነችዋን ኳስ የወሎ ኮምቦልቻ ተጫዋቾች በሰሩት ጥፋት አደገኛ ቦታ ላይ ቅጣት ምት ለቦዲቲ ከተማዎች ተሰጥቷቸዋል። የተገኘውን ቅጣት ምት ሙሉቀን ተስፋዬ ወደግብ ሲመታት የወሎ ኮምቦልቻው ግብ ጠባቂ ለመመለስ ጥረት ቢያድርግም ኳሷ ወጥታ ስትመለስ አሸናፊ መሸሻ በ90+2 ደቂቃ ላይ ወደግብነት ቀይሯታል።  ጨዋታውም 2ለ1 በሆነ ውጤት በቦዲቲ ከተማ በላይነት ተቋጭቷል።

የመጀመሪያ ዙር ማገባደጃ የሆነው ተጠባቂው ጨዋታ በነጥብ ተቀራራቢ የሆኑትን ነጌሌ አርሲን ከሸገር ከተማ አገናኝቷል።

ሳቢ የነበረው ይሄኛው መርሃ ግብር  የመጀመሪያ ግብ እስኪትቆጠር ድረስ ተመጣጣኝ ፉክክር አስመልክቷል። ሁለቱም ቡድኖች ግብ አስቆጥረው ቀዳሚ ለመሆን በተደጋጋሚ ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በመሄድ አስቆጪ የሚባሉ ለግብ የተቃረበ ሙከራ አድርገዋል።

በ18ኛው ደቂቃ የሸገር ከተማው ሚራጅ ሰፋ እና የነጌሌ አርሲው አቤል ፋንታ እርስ በርስ በገቡት እሰጥ አገባ ሁለቱም ለቀይ ካርድ ሰላባ ሆነው ከሜዳ በመሰናበታቸው ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በጎዶሎ ተጫዋቾች ለመጫወት ተገደዋል።

በ33ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ የነጌሌ አርሲው ግዙፉ አጥቂ ታምራት ኢያሱ በግንባሩ ገጭቶ የሸገር ተከላካዮች ሲመልሱበት ድጋሚ አየር ላይ እንዳለች ኳሷን አግኝቷት ከመረብ ጋር አገናኝቶ ነጌሌ አርሲዎችን መሪ አድርጓል።

ነጌሌ አርሲ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ አድርጓል። በ40ኛው ደቂቃ ሙሉቀን ተስፋዬ ከርቀት የመታትን ኳስ የሸገሩ ግብ ጠባቂ እንዴትም ሆኖ አድኗታል። የመጀመረያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ተጨማሪ በታየው ውስጥ ሸገር ከተማዎች ምናልባትም አቻ ሆነው ወደመልበሻ ክፍል መመለስ ሚችሉበትን አጋጣሚ አግኝተው የነጌሌ ተከላካዮች እንዴትም ብለው አድነውባቸዋል። በዚህም የመጀመሪያ አጋማሽ በነጌሌ አርሲዎች 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተጠናክረው የገቡት ሸገር ከተማዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ57ኛው ደቂቃ አረጋ ማሩ ከመስመር ያሻማትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ፋሲል አስማማው አስቆጥሮ አቻ እንዲሆኑ አድርጓል። የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በመነቃቃት የተጫወቱት ሸገሮች በ67ኛው ደቂቃ ጥሩ የግብ ሙከራ አድርገው ለትንሽ ከግብ አግዳም በኩል አልፋባቸዋለች።

ነጌሌ አርሲዎችም ሌላ ግብ ለማስቆጠር ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በ69ኛው ደቂቃ ታምራት ኢያሱ በግንባር ገጭቶ ለትንሽ በግብ አግዳም በኩል ያለፈችበት ኳስ ትታወሳለች። ሆኖም ግን በ75ኛው ደቂቃ አባተ ዓለሙ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶባቸው ቀሪውን 15 ደቂቃ በዘጠኝ ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል።

በዚህም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተገባዷል።  ውጤቱን ተከትሎ ተጋጣሚዎቹ ወደ መሪው አርባምንጭ ለመቅረብ ነበራቸውን ዕድል አምክነዋል። በመሆኑም አርባምንጭ ከተከታዩ ነጌሌ አርሲ ጋር ያለው ልዩነት ወደ አምስት ከፍ በሏል።