ታዳጊ ሉሲዎቹ ከዓለም ዋንጫ ውጪ ሆነዋል

ሞሮኮን የገጠመው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ በተደረገው የመልስ ጨዋታ 1ለ0 ማሸነፍ ቢችልም በድምር ውጤት 2ለ1 ተረቶ ከዓለም ዋንጫው ውጪ ሆኗል።


ሞሮኮ ላይ በሞሮኮ የ 2ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲደረግ 9 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ ጥሩ ፉክክር በተደረገበት እና ዘጠኝ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች በተደረጉበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሞሮኮዎች ጨዋታውን በጀመሩበት ቅጽበት በሁለት ንክኪዎች ብቻ ባደረጉት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ የሉሲዎቹን የግብ ክልል መፈተን ጀምረዋል።

መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ ቀስ በቀስ በኳስ ቁጥጥሩ እየተሻሻሉ በመሄድ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ኢትዮጵያዊያኖች 24ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ዕድላቸውን ፈጥረው እሙሽ ዳንኤል ከሳጥን አጠገብ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ኢነስ ሶውኢፊ መልሳባታለች። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም የግራ መስመር ተከላካይ የሆነችው እፀገነት ግርማ ከረጅም ርቀት አስደናቂ ሙከራ አድርጋ በግብ ጠባቂዋ እና በግቡ የላይ አግዳሚ ተመልሶበታል።

ባልተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መታተራቸውን የቀጠሉት ታዳጊዎቹ ሉሲዎች 30ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ንግሥት በቀለ የሞሮኮ ተከላካዮች በትክክል ባላራቁት ኳስ ጥሩ የግብ ዕድል አግኝታ ከፍ አድርጋ (ቺፕ) ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ኢነስ ሶውኢፊ በጥሩ ንቃት አቋርጣባታለች።

በተረጋጋ ሂደት እና የኳስ ቁጥጥር ጨዋታውን ያስኬዱት ሞሮኮዎች እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የነበራቸው ጥምረት ውጤታማ አልነበረም። ሆኖም በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ሙከራቸውን 37ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ዶሃ ኤል ማዳኒ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ አበባ አጂቦ መልሳዋለች።

ከዕረፍት መልስ ንቦኝ የንን በቤተልሔም ግዛቸው ቀይረው በማስገባት እና መሃል ሜዳው ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ በማስመለስ አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች 51ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አርያት ኦዶንግ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረችውን ኳስ ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ያገኘችው ፀሐይነሽ ጁላ መረቡ ላይ አሳርፋዋለች።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በኋላ በተሻለ የጨዋታ ግለት ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሉሲዎቹ 62ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ፀሐይነሽ ጁላ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆና ያገኘችው አርያት ኦዶንግ ሳትጠቀምበት ስትቀር ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። አርያት ከማዕዘን ያስጀመረችውን ኳስ መሳይ ተመስገን ከግራ መስመር ስታሻማው ኳሱን ያገኘችው እሙሽ ዳንኤል በግንባር ገጭታ ያደረገችው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶባታል።


አልፎ አልፎ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሞክሩት ሞሮኮዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ ግብ አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ በሚል ሲሻር ያንኑ ኳስ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የወሰዱት ኢትዮጵያዎችም ወርቃማ ዕድል ፈጥረው ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘችው እሙሽ ዳንኤል ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክናዋለች። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በኢትዮጵያ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ሞሮኮ በሜዳዋ 2ለ0 በማሸነፏ 2ለ1 በሆነ የድምር ውጤት በኮሎምቢያ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች።