በሉሲዎቹ አሠልጣኝ እና በጋዜጠኞች መካከል ምንድን ነው የተፈጠረው?

የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል ቡድናቸው በሞሮኮ አቻቸው በድምር ውጤት ከተሸነፈ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ከሰጡ በኋላ የተፈጠረው አለመግባባት ምንድን ነበር?

የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በኮሎምቢያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻው ዙር ማጣሪያ ላይ ደርሶ በሞሮኮ አቻው በድምር ውጤት 2ለ1 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ መሆኑ ይታወቃል። ቡድኑ ዛሬ በሜዳው ያደረገውን ጨዋታ 1ለ0 ከረታ በኋላ በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ከአሰልጣኙ ጋር የድህረ-ጨዋታ ቃለ ምልልስ ካደረጉ በኋላ በአሰልጣኙ ፍሬው ኃይለገብርኤል እና ጋዜጠኞች መካከል አለመግባባት እንደተከሰተ አስተውለናል።

በስፋራው የነበሩት ጋዜጠኞች በየተራ አሠልጣኙን ሙያዊ ጥያቄ እየጠየቁ ባለበት ሰዓት በጥያቄዎቹ ምቾት እንዳልተሰማው የሚገልፅ ማንገራገር ያሰማው አሰልጣኝ ፍሬው ጠንከር ባለ ድምፀት አጥጋቢ ባይሆንም ምላሽ ሰጥቶ ከቃለ መጠየቁ መገባደድ በኋላ ከጋዜጠኞቹ ጋር አግባብ በሌለው እንዲሁም ለሚዲያ በማይመጥኑ ቃላት ኃይለ ቃል ሲለዋወጥ አስተውለናል። ከቃላት መሰናዘር በኋላ ዋና አሠልጣኙ ፍሬው እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኙ ሳዳት ጀማል ከጋዜጠኞቹ ጋር አካላዊ ጉሽሚያዎችን ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ብናይም በስፍራው በነበሩ የፀጥታ አካላት ትብብር የቃላት ልውውጡ ሌላ መልክ ሳይኖረው አልፏል።

* በቀጣይ በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚሰጠውን ምላሽ እና የሚይዘውን አቋም እንደ ሚዲያ እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።