የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 1-0 ሞሮኮ(1-2 ድምር ውጤት)

👉”እኔ ማሰልጠን ነው ስራዬ እንደዚህ አይነት አሉባልታዎች ላይ ብዙም ትኩረት አላደርግም።

👉”እንግዲህ አንተ ያየህበት መንገድ ይለያል እኔ ግን እንደ ባለሙያ……”

👉”አንዳንዴ የበይ ተመልካች የሚባል ነገር አለ…”

👉”ይሄ የአንቺ ሀሳብ ነው የሚሆነው…”

👉”ተጫዋች በ45(90) ደቂቃ ታይቶ አይገመገምም…”

👉”…..ይህን ለእኔ ብተውት የተሻለ ይሆናል።

አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ቡድናቸው በድምር ውጤት ከዓለም ዋንጫው ከቀረበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በሰጣ ገባዎች የተሞላ ድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቅን ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው

“ያው የእንግዲህ ዛሬውን ጨዋታ አሸንፈናል ፤ ተጫዋቾቼ በጣም የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል ነገርግን ያገኘናቸውን የግብ እድሎች መጠቀም ያለመቻላችን ከዓለም ዋንጫው አስቀርቶናል። በጨዋታው የተሻለ ትውልድ የታየበት ጨዋታ ነው ብዬ ነው የማስበው ፤ ጥሩ ወጣት ተጫዋቾች በዚህ ቡድን አሉ ብዬ አምናለሁ በቀጣይም ሀገር ወክለው የተሻለ ቡድን ለመስራት በቂ ልጆች የፈሩበትም ነው ብዬ አስባለሁ።”

በጨዋታው ቡድኑ ከወትሮው አንፃር ደካማ ሆኖ ስለመቅረቡ

“እንግዲህ አንተ ያየህበት መንገድ ይለያል እኔ ግን እንደ ባለሙያ ግን አምስት ስድስት እድል አግኝተዋል ፤ አንድ ቡድን አራት አምስት እድል ከፈጠረ ምናልባት በእግርኳስ አንድ ቡድን ምን ያህል እድል መፍጠር እንዳለበት ኮታውን ባላውቀውም ነገርግን የተገኙ እድሎችን መጠቀም አለመቻል በራሱ አንድ አሉታዊ ተፅዕኖ ሆኖ ቢታይም ግን የተሻሉ ነገሮችን ፈጥረዋል ብዬ አምናለሁ ነገርግን ማስቆጠሩ ላይ ችግር ነበረብን እንደ ቡድን ደግሞ ለእሱ እኔ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ።”

የወጣት ቡድኑ ጉዞ በሀገሪቱ እግር ኳስ ላይ ስለሚኖረው ትርጉም

“በተከታታይ እዚህ ምዕራፍ ላይ ደርሻለሁ ፤ ይህም የተሻለ ትውልድ ስለመኖሩ ማሳያ ነው።እኔ ብቻዬን የምሰራው ነገር አይደለም ተጫዋቾቼ ሊመሰገኑ እና ሊከበሩ ይገባል።በነገራችን ላይ ተጫዋቾቼ ሞሮኮን ብቻ አይደለም የገጠሙት ብዙ ፈተናዎችን ነው በዚህ ጨዋታ የገጠሙት።በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ ይህን ውጤት በማምጣታቸው ተጫዋቾቼን ማመስገን እፈልጋለሁ።አንዳንዴ የበይ ተመልካች የሚባል ነገር አለ አንተ እግር ኳሱን ነው የምትመለከተው ከልጆቹ በስተጀርባ ያለውን ነገር አታውቅም በቀጥታ እግር ኳሳዊ ነገሩን መመልከት ብቻ አይደለም ሴቶች ናቸው ብዙ ፈተናዎች አሉ እንደ ወንዶቹ ልጆቹን ጠብቀህ በፈለካቸው መጠን ላትጠቀምባቸው ትችላለህ። ከውስጥም ከውጭም ያሉ ፈተናዎችን ተቋቁመው እንደ ሀገር በመታገላቸው ሊከበሩና ሊመሰገኑ ይገባል።ስህተታቸውን ብቻ አጉልተህ በመናገርህ ትንሽ ተሰምቶኛል ልታሞግሳቸው ነበር የሚገባው።”

አጠቃላይ ቡድኑ ስለገጠመው ውስጣዊ እና ውጭያዊ ችግሮች

“እሱ ሌላ ጉዳይ ነው ፤ እዚህ ጋር ስላለው ነገር ነው እኔ ያነሳሁት ወደ ሌላ ጉዳይ ስትሄድ እሱ ሌላ ጥያቄ ነው።”

ስለአርያት የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ

“የአርአያትን ኳሊቲ እንደ ባለሙያ እኛ እናውቀዋለን ፤ ስንጠብቃት የነበረበት መንገድ አለ። ተጫዋች በ45(90) ደቂቃ ታይቶ አይገመገምም እኛ የጠብቅነው ነገር ነበር ያንን ኳሊቲ እስከመጨረሻው የመጠበቅም ሆነ ያለመጠበቅም የባለሙያው ነው የሚሆነው የተመልካቹ ሳይሆን የእኔ ስለሚሆን ይህን ለእኔ ብተውት የተሻለ ይሆናል።”

ከጨዋታው በፊት ባልተለመደ መልኩ ለተጋጣሚ ቡድን አባላት ስለተሰጠው ሽልማት ምክንያት

“ሰዎችን ማክበር የኢትዮጵያ ልማድ ስለሆነ አክብረናቸው እነሱም እዛ አክብረው ስላስተናገዱን ያንን በማሰብ አክብረን የመጡትን አምባሳደሮቹን የኢትዮጵያን ባህል ለማሳየት ያንን አድርገናል።”

በሞሮኮ ከሞሮኮ ሰዎች ጋር “ተፈጠረ” ስለተባለው ግጭት እና ስለሚኖረው ተፅዕኖ

“ይሄ የአንቺ ሀሳብ ነው የሚሆነው ፤ ፀብም የለም ምንም የለም በወቅት በስፍራው የነበረነው እኛ ነን። የነበረው ነገር እግር ኳሳዊ መንገድ ነው የነበረው ነገር ከደጋፊ መስሎን ነበር ፀብ ሳይሆን ቀለል ባለ መንገድ የነበረ አለመግባባት ነው።ሞሮኮ እና ኢትዮጵያ ጥሩ ግንኙነት አላቸው እኔም በግሌ ሁለት ሶስቴ ሄጃለሁ ባለመተዋወቅ የተፈጠረ ከዛ በኃላ ይቅርታ ተባብለህ የሚታለፍ ነገር አይነት ነው የተፈጠረው። በሌለሽበት ግን ይህን በማምጣትሽ እንዳለሽ ሆነሽ ነው ያወራሽው እኔ ማሰልጠን ነው ስራዬ እንደዚህ አይነት አሉባልታዎች ላይ ብዙም ትኩረት አላደርግም። እኔ በምንም ውስጥ የለሁም ጭቅጭቅ ነው የነበረው እግር ኳስ አንዱ ባህሪው ደግሞ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነህ ልትነጋገር ትችላለህ።”

ከሜዳ ውጭ ስለነበሩ ችግሮች

“እሱን ፌደሬሽኑ በሚያዘጋጀው መግለጫ ላይ ያኔ እሰጣለሁ።”