መረጃዎች | 46ኛ የጨዋታ ቀን

ሊጉ ከቀናት ዕረፍት በኃላ ነገ በ12ኛ የጨዋታ ሳምንት ሲመለሰ የነገዎቹን ሁለት መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከሻሸመኔ ከተማ

በ9 ነጥቦች በሰንጠረዡ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያ መድኖችን በ7 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሻሸመኔ ከተማዎች የሚያገናኘው ጨዋታ የሳምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ ነው።

አምና በሊጉ ሳይጠበቁ እጅግ አስደናቂ ዓመትን በማሳለፍ በሶስተኝነት ሊጉን ማጠናቀቅ ችለው የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች የ2016 የውድድር ዘመን ግን እንደ ዳገት ከብዷቸው እየተመለከትን እንገኛለን ፤ አምና በዚህ ጊዜ 22 ነጥቦችን በመሰብሰብ በሰንጠረዡ አናት ይፎካከር የነበረው ቡድኑ አሁን ላይ ከወራጅ ቀጠናው በግብ ክፍያ ብቻ ርቆ ይገኛል።

በእንቅስቃሴ ረገድ አውንታዊ እግር ኳስን ለመጫወት እየሞከረ የሚገኘው ቡድኑ በቂ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሆነ ሳጥናቸውን በመከላከል ረገድ በብዙ መልኩ ውስንነቶች ያሉበት ቡድን ሆኖ እየተመለከትን እንገኛለን።በመጨረሻ ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት መድኖች የመጀመሪያ ዙሩን በተሻለ መልኩ ለመፈፀም ከቀሪ ሶስት ጨዋታዎች የተሻለ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአንፃሩ በመጨረሻ አራት የሊግ መርሃግብራቸው ምንም ሽንፈትን ያላስተናገዱት ሻሸመኔ ከተማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት እንደ ሰማይ ርቋቸው ከነበረው ድል ጋር ታርቀዋል ፤ በእንቅስቃሴ ረገድ እየተሻሻለ የሚገኘው ቡድኑ ሀምበሪቾን ድል ሲያደርግ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር መሆኑ ለቡድኑ ከፍ ያለ የራስ መተማመንን እንደሚያላብስ ይጠበቃል።

ቡድኑን ከመሸነፍ ስነልቦና ማውጣት ወሳኙ የቤት ስራቸው እንደሆነ ደጋግመው ሲናገሩ የነበሩት አሰልጣኝ ዘማርያም አሁን ላይ ይህን የውድድር ዘመናቸውን የመጀመሪያ ድል እንዴት ይጠቀሙበታል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተወገደው ያሬድ ካሳዬ በስተቀር የተቀረው ስብስብ ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።በአንፃሩ በሻሸመኔ ከተማዎች በኩል እጁ ላይ ጉዳት ካስተናገደው ቻላቸው መንበሩ በስተቀር የተቀረው ስብስብ ለነገ ጨዋታ ዝግጁ ነው።

ቢንያም ወርቅአገኘሁ በመሐል ዳኝነት ለዚህ ጨዋታ ሲመደብ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና አማን ሞላ በረዳትነት አዲሱ የሊጉ ዳኛ መስፍን ዳኜ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይሟል።

ከ16 ዓመታት የኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኞች በሊጉ ሦስት ጨዋታ ላይ የተገናኙ ሲሆን የመጀመርያው በመድን 1-0 አሸናፊነት፣ ሁለተኛው በሻሸመኔ 2-1 አሸናፊነት፣ ሦስተኛው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።


መቻል ከፋሲል ከነማ

የጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ መርሃግብር አመሻሽ 12 ሰዓት ሲል በውድድር ዘመኑ ፍፃሜ በሰንጠረዡ አናት ለዋንጫ እንደሚፎካከሩ የሚጠበቁትን ሁለቱን ቡድኖች ያገናኛል።

በእኩል 26 ነጥቦች በግብ ተበላልጠው ሊጉን በሁለተኛነት እየመሩ የሚገኙት መቻሎች የዘንድሮው የውድድር ዘመናቸው ጉዞ እጅግ አስደናቂ ሆኗል ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጠንካራ ስብስብ ባለቤት ቢሆኑም ስብስቡን የሚመጥን ውጤት ለማምጣት ተቸግረው የነበሩት መቻሎች ዘንድሮ ግን በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመሩ እጅግ ምርጥ የሚባል የመጀመሪያ ዙርን እያሳለፉ ይገኛሉ።

ከሌሎች ቡድኖች በተሻለ ከተለያዩ የሜዳ ክፍሎች ግቦችን እያገኙ የሚገኙት መቻሎች በተለይ የመሀል ክፍላቸው ኳሶችን አመቻችቶ ከማቀበል ባለፈ በግቦች ላይ የተሻለ ተሳትፎን እያደረጉ ይገኛል በተለይም ከነአን ማርክነን የቡድኑ ማጥቃት ላይ ያለው ተፅዕኖ እየጎላ ይገኛል።

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እንደ አዲስ እየተገነቡ የሚገኙት ፋሲሎች ወጥ ለመሆን ተቸግረው ቢስተዋሉም በ18 ነጥቦች አሁን ላይ በሰንጠረዡ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ፤ ይህም ከወዲሁ ከሰንጠረዡ አናት ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ያላቸው ልዮነት 8 ነጥብ የመሆኑ ጉዳይ ለፋሲሎች አሳሳቢ ይመስላል።

ነገም በሰንጠረዡ አናት ከሚገኝ ቡድን ጋር በሚያደርጉት በዚህ ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ መውሰድ ከቻሉ ለእነሱ የሚኖረው ትርጉም የላቀ መሆኑ ተከትሎ ከፍ ባለ አላማ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በመቻሎች በኩል ሙሉ ስብስቡ ለነገ ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ሲረጋገጥ በፋሲል ከነማዎች በኩል ደግሞ አማኑኤል ገብረሚካኤል ፣ እዮብ ማቲያስ እና ፍቃዱ አለሙ ልምምድ ቢጀምሩም መሰለፋቸው ሲያጠራጥር የመስመር ተከላካዩ ዓለምብርሀን ይግዛው ደግሞ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 11 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ስድስት ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖራቸው መቻል ሦስት ጨዋታዎች አሸንፏል። ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ናቸው። ፋሲል 16 ሲያስቆጥር መቻል 8 አስቆጥሯል።

ይህን ተጠባቂ ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ማዕደር ማረኝ በረዳት ዳኝነት ባህሩ ተካ በአንፃሩ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተሰይሟል።