የአሰልጣኞች አስተያየት | መቻል 0-0 ፋሲል ከነማ

“ፋሲል ትልቅ ፤ ለዋንጫ የሚወዳደር ቡድን ነው። ከዚህ ቡድን ጋር በጎዶሎ መጫወት የተጫዋቾቼን ጥንካሬ ያሳያል” ገብረክርስቶስ ቢራራ

“በምንችለው መጠን ነጥብ ይዘን ለመውጣት ሞክረናል። እነሱም ነጥብ ይዞ ለመውጣት የሚችሉትን አድርገው ወተዋል ፤ ተሳክቶላቸዋል” ውበቱ አባተ

ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል

የጨዋታው እንቅስቃሴ እንደለት ነበር?

ጨዋታው ጠንካራ ጨዋታ ነው። ፋሲል ትልቅ ፤ ለዋንጫ የሚወዳደር ቡድን ነው። ከዚህ ቡድን ጋር በጎዶሎ መጫወት የተጫዋቾቼን ጥንካሬ ያሳያል።

ቀይ ካርዱ ያሰቡት የጨዋታ እቅድ ላይ ስለነበረው ተፅዕኖ…?

ጎዶሎ መሆናችን ከጨዋታ መንገዳችን እንድንወጣ አድርጎናል። ምክንያቱም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ነበርን። ነገርግን አንድ ተጫዋች ሲጎልብህ የግድ ሌላ አጨዋወት ነው የምትመርጠው። ስለዚህ ወደ ራስህ ሜዳ አዘንብለህ ስለምትጫወት ያ ነገር ከአጨዋወታችን ውጪ አድርጎናል።

ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጥሩ ነበር። ከሌላው ጊዜ በተለይ በስሜት ትልቅ ጨዋታ የሚመስል ጨዋታ ሙሉ 90 ደቂቃ ለመጫወት ሞክረናል። የምንችለውን ኳስ መቆጣጠሩንም፣ ወደ ፊት መሄዱንም፣ እድል መፍጠሩንም ከሌሎቹ ቀኖች በተሻለ ለማድረግ ሞክረናል። ግን በመከላከያ በኩልም ጠንካራ ተጋጣሚያችን ነበር ምንም እንኳን አንድ ልጅ ቢጎልባቸውም በጥልቀት ወደ ኋላ ተመልሰው መከላከል ከመምረጣቸው አንፃር በቂ የሚባል ዕድሎችን ፈጥረናል። እንደዚህ አይነት ቲም ላይ ወደታች ወርዶ እየተጫወተ አስከፍቶ ማግባት ከባድ ነገር ነው። በተጨማሪም ሜዳው ለዛ የሚሆን አይደለም። እነሱ ወደ ታች ወርደው ነበር የሚጫወቱት፣ እኛን በመልሶ ማጥቃት ጠብቀው ነበር ለማጥቃት የሚሞክሩት። በዚህ በኩል ይሄንን መጠበቅ አለብህ በዛ በኩል ያንን አስከፍተህ ማግባት አለብህ። በአጠቃላይ 90 ደቂቃው ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል።

የቁጥር ብልጫውን ለመጠቀም ስላሰቡት መንገድ

መጀመሪያ በሁለት የተከላካይ አማካይ ነበር የገባነው በኋላ ግን ከ1 ሰዓት በኋላ አንድ የመከላከል ባህሪ ያለው ተጫዋች ብቻ በመጠቀም የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች አስገብተናል። በዛ ላይ ደግሞ እድሎች ለመፍጠር ያንን የተዘጋውን ቦታ የቁጥር ማነስ ስላለው ያንን ለመጠቀም ሞክረናል። ለመስራት ተሞክሯል። በጣም በጣም ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት ነበር። በተጨማሪም ጨዋታው ቶሎ ቶሎ ይቆራረጥ ስለነበር ከቴምፖ ያወጣን ነበር። በምንችለው መጠን ነጥብ ይዘን ለመውጣት ሞክረናል። እነሱም ነጥብ ይዞ ለመውጣት የሚችሉትን አድርገው ወተዋል ፤ ተሳክቶላቸዋል። አንዳንድ ጊዜ በቁጥር መጉደል ኢነርጂ ይሰጥካል። ያ ለእኛ ነገሮችን ከባድ አድርጎብናል። እኩል ለእኩል ሆነን ክፍት ጨዋታ ቢሆን የተሻለ ነበር። በተጨማሪም እንደዚህ አይነት ጥብቅ መከላከል ሲመጣ ያንን ከፍተህ መግበት የምትችለው በቅንጅት ቅብብል ነው። ይሄንን ለመጫወት ደግሞ ሜዳው ራሱን የቻለ ተፅዕኖ አለው። በአጠቃላይ ነጥብ ከመጣላችን ውጪ መጥፎ አልነበረም። ተጫዋቾቼ ባሳዩት ጥረትም ደስተኛ ነኝ።