ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል

በሣምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ መቻል እና ፋሲል ከነማ 0-0 ተለያይተዋል።

በምሽቱ መርሐግብር መቻል እና ፋሲል ከነማ ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች ከ11ኛ ሣምንት ጨዋታቸው በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። መቻሎች ድሬዳዋን 3ለ1 ከረቱበት አሰላለፍ አቤል ነጋሽ እና ቺጂኦኬ ናምዲ አኩኔቶን አሳርፈው በረከት ደስታ እና ምንይሉ ወንድሙን ሲተኩ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1ለ0 የተሸነፉት ፋሲሎች በአንጻሩ ቃልኪዳን ዘላለም እና ዮናታን ፍስሃን በዓለምብርሃን ይግዛው እና አቤል እንዳለ ምትክ በማስገባት ለጨዋታው ቀርበዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ሕልፈት ምክንያት የሕሊና ጸሎት ተደርጎ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታውን በተሻለ ግለት የጀመሩት ዐፄዎቹ 8ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አምሳሉ ጥላሁን ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ሆኖ አክርሮ በመምታት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ሲመልስበት የነጠረውን ኳስም የመሃል ተከላካዩ ስቴፈን ባዱ አኖርኬ ተገልብጦ በመምታት አስወጥቶታል።

በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው መቻሎች 10ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን ሲፈጥሩ በረከት ደስታ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ምንይሉ ወንድሙ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

በተጫዋቾች መካከል በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ጉሽሚያዎች ታጅቦ የቀጠለው ጨዋታ 14ኛው ደቂቃ ላይ ቀይ ካርድ ተመዞበታል። የመቻሉ አማካይ በኃይሉ ግርማ ከሱራፌል ዳኛቸው ጋር የዓየር ላይ ኳስ ብልጫ ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት በሠራው ጥፋት እና ሲያርፍም ፊቱን በጫማው በመርገጡ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ ጉዳት የደረሰበት ሱራፌል ዳኛቸውም ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ወደ ጨዋታው ተመልሷል።

በተደጋጋሚ በዋና ዳኛው ፊሽካ እየቆመ በመጠኑ  እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ 33ኛው ደቂቃ ላይ በይሁን እንዳሻው አማካኝነት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ዐፄዎቹ 38ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። ጋቶች ፓኖም ለጌታነህ ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በፍጥነት ከሳጥኑ በመውጣት ኳሱን በግንባር ገጭቶ ለማራቅ ሲሞክር የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግራ እግሩ በጥሩ ዕይታ ቢመታውም ኳሱ ነጥሮ የግቡን አግዳሚ በመምታት ወደ ውጪ ወጥቷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት ሲቀጥል ፋሲሎች የአጋማሹን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ 54ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ቃልኪዳን ዘላለም ከጌታነህ ከበደ በተቀበለው ኳስ መሬት ለመሬት በመምታት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ሲይዝበት በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ የመቻሉ ምንይሉ ወንድሙ የግብ ጠባቂውን ሳማኬ ሚኬልን መውጣት ተመልክቶ ከረጅም ርቀት ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ የማጥቃት ኃይላቸውን ለማጠናከር ጥረት ያደረጉት ዐፄዎቹ 73ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን ሲፈጥሩ ሽመክት ጉግሣ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጌታነህ ከበደ እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ሳይጠቀሙበት ቀርተው ግብ ጠባቂው ሲይዘው ያን ኳስ በመልሶ ማጥቃት የወሰዱት መቻሎች በወሰዱት ኳስ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ከነዓን ማርክነህ እየገፋ ሳጥን ውስጥ ባስገባው ኳስ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

በቀሪ ደቂቃዎችም ጨዋታው መጠነኛ ፉክክር ሲደረግበት ተቀይሮ የገባው የዐፄዎቹ አማካይ ጃቢር ሙሉ 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ከ75 ደቂቃዎች በላይ በጎደሎ የተጫዋቱት መቻሎች ነጥባቸውን 27 በማድረስ ከነገው የንግድ ባንክ ጨዋታ አስቀድሞ በጊዜያዊነት ሊጉን በአንድ ነጥብ ልዩነት መምራት ጀምረዋል።