የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ መድን 1-1 ሻሸመኔ ከተማ

የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን እና ሻሸመኔ ከተማ መካከል ተከናውኖ 1ለ1 ከተቋጨ በኋላ የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን ሲያደርጉ በሻሸመኔ በኩል አሰልጣኙ ቅጣት ላይ ስለሚገኙ ቃለ መጠይቅ ማድረግ አልቻልንም።

አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን

ስለ ጨዋታው…?

“ከሰነበትንበት መቼስ ደህና ነው መጥፎ አይደለም ለእኔ። ተጋጣሚያችን ሙሉ ለሙሉ በመከላከል ላይ ያዘነበለ ጨዋታ ነው ያደረገው ያንን ፔኔትሬት ለማድረግ ጥረት አድርገናል። በተለይ ከዕረፍት በኋላ ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት እና በጋራ ለመሄድ ነበር ሀሳባችን ግን ጥራት ያለው የማጥቃት ሂደታችን ትንሽ ቀንሷል እዛ ላይ መጨረስ አለመቻላችን ነው እንጂ ደህና ነው መጥፎ አይደለም ፣ ቢያንስ አንድ ነጥብም ይዞ መውጣት በራሱ ጥሩ ነው ፣ መሸነፍም ሊኖር ስለሚችል።”

አስቀድመው ጎል ቢያስቆጥሩም አስጠብቀው መውጣት አለመቻላቸው…

“ኳስ ይታወቃል የሆነ ወቅት አለህ ፣ አንዴ የሆነ ነገር ከመጣብህ የሚይዝህ ጊዜ አለው ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሲገባልህ የሚገባበት ጊዜ አለ። ያቺን ወቅት አሁን ማለፍ አልቻልንም አሁን ቢያንስ ጥሩ ነው ከሦስት ጨዋታ በኋላ ነው አንድ ነጥብ ያገኘነው እና እየመራን ያንን ማስጠበቅ አለመቻል ከጭንቀት ፣ ከፍላጎት መብዛት የተነሳ ስህተት ነው እየተፈጠረ ያለው ስለዚህ አንድ ቀን ነገ ፣ ከነገ ወዲያ ደግሞ የተሻለ ነገር ይሠራሉ ብዬ አስባለሁ እና ጥረታቸው መጥፎ አይደለም።”

በጉዳት ተቀይሮ ለመውጣት ስለተገደደው አቡበከር ኑራ…

“ጉዳት እንደማንኛውም ጊዜ ሊያጋጥም ይችላል። የእርሱ ደግሞ ብሊዲንጉ ሊቆም ስላልቻለ የግድ ነው መቀየር ነበረበት ተቀይሯል። እንግዲህ እናየዋለን ወደፊት።”