ሪፖርት | መድን እና ሻሸመኔ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ መድን እና በሻሸመኔ ከተማ መካከል የተደረገው የሣምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

ዛሬ በተጀመረው 12ኛ ሣምንት የዕለቱ ቀዳሚ በነበረው መርሐግብር ኢትዮጵያ መድን እና ሻሸመኔ ከተማ ሲገናኙ መድኖች በ11ኛው ሣምንት በንግድ ባንክ ከተሸነፉበት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። በያሬድ ካሳዬ እና ንጋቱ ገብረሥላሴ ምትክ አዲስ ተስፋዬ እና መስፍን ዋሼ ሲገቡ ሻሸመኔ ከተማ በአንጻሩ በሀምበሪቾ ላይ ድል የቀናው ስብስቡን ዛሬም ለውጥ ሳያደርግበት ቀርቧል።


ቀን 9 ሰዓት ላይ በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ ሻሸመኔዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው በመጫወት በ10 ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ በቅድሚያም 2ኛው ደቂቃ ላይ አለን ካይዋ ከቅጣት ምት ከሴኮንዶች በኋላ እና 10ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሄኖክ ድልቢ ያደረጓቸው ሙከራዎች ሁለቱ በግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ሲያዙ አንዱ የሄኖክ ሙከራም በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ ቢወስዱም የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የተቸገሩት መድኖች 21ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት የገጠመውን መሐመድ አበራን አስወጥተው አቡበከር ወንድሙን ለማስገባት ሲገደዱ የአጋማሹን የተሻለ ለግብ የቀረበ ሙከራም 23ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። መስፍን ዋሼ በቀኝ መስመር በግሩ እግሩ አክርሮ የመታው ግሩም ኳስ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

በጥቂት ንክኪዎች ከራሳቸው የግብ ክልል በመውጣት በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ያስቀጠሉት ሻሸመኔዎች 30ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት የገጠመውን አሸናፊ ጥሩነህን በማስወጣት ኢዮብ ገብረማርያምን ሲያስገቡ የጋለው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በመጠኑ እየተቀዛቀዘ ቢሄድም በምንተስኖት ከበደ የሚመራው የተከላካይ መስመራቸው ጥንካሬም ጎልቶ ታይቷል።


ከዕረፍት መልስ ተሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ መድኖች 53ኛው ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር ተከላካዩን አብዱልከሪም መሐመድን አስወጥተው አቡበከር ወንድሙን በእርሱ ቦታ ወደኋላ በመመለስ አጥቂውን ቹኩዌሜካ ጎድሰንን ሲያስገቡ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርገዋል።

ጨዋታው 66ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ መድኖች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ብሩክ ሙሉጌታ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ በመሆን ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ቹኩዌሜካ ጎደሰን ከነካው በኋላ ያገኘው ወገኔ ገዛኸኝ የመታው ኳስ በተከላካይ ተጨርፎ መረቡ ላይ አርፏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ራሳቸው ግብ ተጠግተው መጫወትን የመረጡት ሻሸመኔዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ግን ወደፊት ተጭነው መጫወት በአራት ደቂቃዎች ልዩነት የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ሀብታሙ ንጉሤ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ የተመለሰውን ኳስ ያገኘው አብዱልቃድር ናስር ግብ አድርጎታል። ግቡ በተቆጠረበት ቅጽበትም የመድኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ ጉዳት አስተናግዶ በተመስገን ዮሐንስ ተተክቷል።

በቀሪ ደቂቃዎችም መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ በተጨመሩ 8 ደቂቃዎች ውስጥ ይበልጥ ተጋግሎ ሲቀጥል መድኖች 90+3ኛው ደቂቃ ላይ ወርቃማ የግብ ዕድል ፈጥረው አቡበከር ወንድሙ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ብሩክ ሙሉጌታ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ በድንቅ ቅልጥፍና መልሶበታል። ሆኖም ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።