​የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለመልስ ጨዋታ ነገ ወደ ኬንያ ያመራል

በ2018 ፈረንሳይ ለምታስተናግደው ከ20 አመት በታች ሴቶች የአለም ዋንጫ የመጀመርያው ዙር የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ነገ ወደ ኬንያ ያቀናል፡፡

በአሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ የሚመራዉ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ጨዋታውን ሀዋሳ አለም አቀፍ ስታድየም አድርጎ በምርቃት ፈለቀ እና አለምነሽ ገረመው የመጀመርያ አጋማሽ ሁለት ጎሎች 2-0 መምራት ቢችልም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ጎሎች 2-2 በመውጣት በመልሱ ጨዋታ የማለፍ እድሉን አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ ያለፉትን አስር ቀናት በሀዋሳ ከተማ በጨዋታው ባሳዩት ደካማ ጎን ላይ አተኩው ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በእነዚህ ቀናት ወደ ቀጣዩ የማጣርያ ዙር ለማለፍ የሚያስችለውን ውጤት ለማስመዝገብ የቡድኑ አባለት የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ተነሳሽነት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

26 የልኡካን ቡድን በመያዝ ነገ ማለዳ ወደ ኬንያ የሚያቀናው ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመርያው ጨዋታ ከነበሩት 18 ተጨዋቾች ውስጥ ብሩክታዊት አየለ ተቀንሳ ገነሜ ወርቁ ተከታታለች፡፡

የቡድን ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች

ትግስት አበራ ፣ እምወድሽ ይርጋሸዋ

ተከላካዮች

ቅድስት ዘለቀ ፣ አረጋሽ ፀጋዬ ፣ ባንቺአየሁ ታደሰ ፣ ቤቴልሄም ከፍያለው ፣ ምህረት መለሰ ፣ ገነሜ ወርቁ

አማካዮች

እመቤት አዲሱ ፣ ሜላት ደመቀ ፣ አለምነሽ ገረመው ፣ ጤናዬ ወሜሴ ፣ የምስራች ላቀው ፣ ዘይነባ ሰይድ ፣ ፅዮን ፈየራ

አጥቂዎች

ምርቃት ፈለቀ ፣ ሴናፍ ዋቁማ ፣ ትመር ጠንክር

ጨዋታው ቅዳሜ በማቻኮስ የሚደረግ ሲሆን ጨዋታውን የሚመሩ ዳኞች ዩጋንዳዊያኑ አና አኮዪ ፣ ዶከስ አቱሀይሬ እና ጃኔ ሙቶንዪ ናቸው፡፡ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች አሸናፊ በቀጣይ የጋና እና አልጄርያ አሸናፊን የሚገጥም ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *