ሪፖርት | ዐፄዎቹ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል

ፋሲል ከነማ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ድል ሻሸመኔ ከተማን 2ለ0 በመርታት አስመዝግበዋል።

ፋሲል ከነማ ከመቻል ጋር ያለ ጎል አቻ ካጠናቀቁበት ጨዋታ የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን ዮናታን ፍሰሀ ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ጋቶች ፓኖምን አስወጥተው በምትካቸው ዓለምብርሀን ይግዛው ፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ኤልያስ ማሞ ሲተኩ በአንፃሩ ሻሸመኔዎች ደግሞ ከኢትዮጵያ መድን ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታቸው የተጠቀሙትን ቋሚ አሰላለፍ ሳይለውጡ ዛሬም ቀርበዋል።

ዝግ ባለ እንቅሰቃሴ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ፈጣን ሙከራን ገና በ3ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ያስመለከተን ፤ አሸብር ውሮ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ያቀበለውን ኳስ ሀብታሙ ንጉሴ በግራ እግሩ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ ቢመታም ሚክኤል ሳማኪ ያዳነበት አጋጣሚ የጨዋታው የቀዳሚ ሙከራ ነበረች።

ሁለቲ ቡድኖቹ መርጠው የገቡትን የጨዋታ አቀራረብ በግልፅ ለመረዳት የግድ ደቂቃዎች ለመጠበቅ በተገደድንበት በዚሁ ጨዋታ ዐፄዎቹ ወደ ቀኝ የሜዳው ክፍል አጋድለው በተለይ ሱራፌል ዳኛቸውን መነሻ ካደረጉ ኳሶች የሽመክት እና ዓለምብርሀንን ጥምረት በመጠቀም ለማጥቃት ቢሞክሩም የሻሸመኔን የመከላከል መዋቅር በማለፉ ረገድ ግን ውጤታማ አልነበሩም።

በፈጣን የመልሶ ማጥቃትን እና ከሁለቱ መስመሮች ወደ ሳጥን በሚሻገሩ ኳሶች ለማጥቃት የጣሩት ሻሸመኔዎች በአጋማሹ ሁለተኛ ሙከራዎችን ሰንዝረዋል ፤ በ19ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር መነሻውን ባደረገ ማጥቃት ሀብታሙ ንጉሴ ያቀበለውን ኳስ አብዱልቃድር በቀጥታ ቢመታም ኳሷ የግቡ ቋሚ ብረትን ታካ የወጣችበት አጋጣሚ በጣም አደገኛዋ ነበረች።

ከሚያደርጓቸው ቅብብሎች ውጪ ከጎል ጋር ለመገናኘት የሚሄዱበት አካሄድ የተቀዛቀዘባቸው ፋሲሎች 37ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ባደረጋት እና ኬኒ ሰይዲ በመለሰበት አጋጣሚ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ማድረግ ሲችሉ የተቀዛቀዘ ፉክክርን ያስመለከተን አጋማሽ ያለ ጎል ተገባዷል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ፋሲሎች ዓለምብርሀን ይግዛውን በአማኑኤል ገብረሚካኤል በተኩ ደቂቃዎች ልዮነት ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። በ48ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው ሳማኪ በረጅሙ የለጋውን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል በፍጥነት ወደ ሻሸመኔ የተከላካይ ክፍል የማሳለፉን ተከትሎ ምንተስኖት ከበደ ኳሷን ሊማውጣት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ተከትሎ ከጀርባው የነበረው ጌታነህ ኳሷን አግኝቶ ከግብ ክልሉ የወጣውን ግብ ጠባቂው ኬኒ ሰይዲን ጭምር በማለፍ መረቡ ላይ ኳሷን አሳርፏታል።

የተጫዋች ለውጥን ካደረጉ በኋላ ተቀይሮ በገባው እና በግራ በኩል በተሰለፈው አማኑኤል አማካኝነት አፄዎቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት ተሳትፎን ለማድረግ ሲጥሩ አስተውለናል።

ከሳጥን ውጪ ከርቀት በሚደረጉ ሙከራዎች ጥቃቶችን ለመሰንዘር የሞከሩት ሻሸመኔ ከተማዎች 52ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አለን ካይዋ አክርሮ መቶ ሳማኪ በአግባቡ የተቆጣጠረበት መልካሟ የቡድኑ አጋጣሚ ነበረች። የመጨረሻዎቹን ሀያ ደቂቃዎች በእጅጉ ወረድ ባለ ፉክክር ውስጥ ሆኖ የቀጠለው የቡድኖች ጨዋታ ጥራት ያላቸውን ሙከራዎች ከመመልከት ይልቅ ቅብብሎችን በርከት ያሉ ቅብብሎችን ያስተዋልንበትም ነበር።

መነሻዋን ከይሁን ያደረገው የማጥቃት ሂደት ጌታነህ ከበደ መሬት ለመሬት ወደ ውስጥያሻገረውን ኳስ በትላንትናው ዕለት ሁለተኛ ልጁን ያገኘው ጋቶች ፓኖም ከመረብ በማዋሀድ በመጨረሻም ጨዋታው በፋሲል ከነማ የ2ለ0 ድል አድራጊነት እንዲቋጭ አስችሏል ፤ ድሉን ተከትሎ ፋሲሎች ስድስተኛ ድላቸውን በማሳካት በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ላይ ሲቀመጡ ሻሸመኔዎች በአንፃሩ በሊጉ ሰባተኛ ሽንፈታቸውን ተጎንጭተዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሻሸመኔው ረዳት አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ ሁለቱም አርባ አምስቶች ላይ ቡድናቸው ጥሩ መንቀሳቀሱን ጠቁመው ውጤቱን የቀየረው ግን ጌታነህ ያስቆጠራት ግብ በተጫዋቾቻቸው ስህተት መሆኑ ለውጤቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን ሲናገሩ በአንፃሩ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በሁለቱም አርባ አምስት ጥሩ ተጫውተናል ካሉ በኋላ በተቻለ መጠን ኳሶችን ተቆጣጥረን በዕርጋታ ለመሄድ ጥረት በሚደረግበት ወቅት መጣደፎች እንደነበሩ እና ሜዳውም ለጨዋታ ምቹ አለመሆኑን ገልፀዋል።