ሪፖርት | ሀይቆቹ ድል አድርገዋል

ሀዋሳ ከተማዎች በዓሊ ሱሌይማን እና አዲሱ አቱላ ግቦች የውድድር ዓመቱ አራተኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

ወልቂጤ ከተማዎች በመጨረሻው ጨዋታ በቋሚ ከተጠቀሟቸው ተጫዋቾች መድን ተክሉ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና ስንታየሁ መንግስቱ በዳንኤል ደምሱ፣ ተመስገን በጅሮንድ እና ሳምሶን ጥላሁን ተክተው ሲገቡ ሀዋሳዎች በበኩላቸው ደግሞ በአዳማ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ ቻርለስ ሉክዋጎ፣ እንየው ካሳሁን እና ሰለሞን ወዴሳን በፅዮን መርዕድ፣ በረከት ሳሙኤል እና ሲሳይ ጋቾ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ሁለቱም ቡድኖች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ በሚያደርጓቸው ያልተሳኩ ሙከራዎች ታጅቦ የጀመረው ይህ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥቂት የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበር።

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ለኳስ ቁጥጥር ቅድምያ ለመስጠት ሲታትሩ የተስተዋሉት ሀዋሳዎች ብዙም ሳይቆዩ አጨዋወታቸውን ወደ ፈጣን የመልሶ ማጥቃትና ቀጥተኛ አጨዋወት ሲቀይሩ ወልቂጤዎች ግን ምንም እንኳ የጠሩ የግብ ዕድሎች ባይፈጥርላቸውም ኳሱን በተሻለ መንገድ ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል።

ቀዝቃዛ የማጥቃት እንቅስቃሴ በነበረበት የመጀመርያው አጋማሽ ሀዋሳዎች በበረከት ሳሙኤል ወልቂጤዎች ደግሞ በተመስገን በጅሮንድ በተመሳሳይ በግምባር የተገጩ ሙከራዎች አድርገዋል። አቡበከር ሳኒ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ ያደረገው ደካማ ሙከራም በመጀመርያዎች ደቂቃዎች ከተፈጠሩ ዕድሎች የተሻለ ለግብ የቀረበ ነበር።

ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር የመሀል ሜዳውን ብልጫ ለመውሰድ ያልተቸገሩት ወልቂጤዎች በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ይዘውት የገቡትን ኳስ ጋዲሳ መብራቴ ካመከናት ሙከራ በኋላ በሀያ ሰባተኛው ደቂቃ በአቡበከር ሳኒ አማካኝነት ጨዋታውን የሚመሩበት ዕድል አግኝተዋል።

አጥቂው ሳምሶን ጥላሁን በጥሩ መንገድ አሾልኮት ጋዲሳ መብራቴ የጨረፈውን ኳስ አግኝቶ ነበር ወደ ግብነት የቀየረው።

ከግቡ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ያልዘገዩት ሀዋሳ ከተማዎችም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። የሀይቆቹ ፈጣን አጥቂ ዐሊ ሱሌይማን ከሳጥኑ አካባቢ ያገኛትን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከተከላካዮች በማምለጥ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ቀዝቃዛና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ሁለተኛው አጋማሽ በብዙ መለክያዎች የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ሆኖም አጋማሹ በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃዎች ልዮነት ሀዋሳዎች በአዲሱ አቱላ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል፤ የመስመር ተጫዋቹ ከግራ መስመር በግሩም ሁኔታ የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ አጨራረስ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው።

ተመስገን በጅሮንድ ከቅጣት ምት፤ አቡበከር ሳኒ ደግሞ ከመዓዘን ምት የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ያደርገው ሙከራ ሰራተኞቹን አቻ ለማድረግ የተቀረቡ ነበሩ። ጨዋታውን የሚመሩበት ግብ ካገኙ በኋላ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት አፈግፍገው ለመጫወት የመረጡት ሀይቆቹ በረከት ሳሙኤል ከረዥም ርቀት ካደረጋት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩትም አቤኔዘር ዮሐንስ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲወገድ መደበኛ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩ ሰባት ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ወልቂጤዎች ግብ ለማስቆጠር በርካታ ጥረቶች ቢያደርጉም ጥሩ ቀን ያሳለፈውን የሀዋሳ የተከላካይ መስመር አልፈው ማስቆጠር አልቻሉም። ይህንን ተከትሎ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ የሁለት ለአንድ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ወልቂጤዎች ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች ስድስተኛ ሽንፈት ቀምሰዋል።