መረጃዎች | 53ኛ የጨዋታ ቀን

የአስራ ሦስተኛው ሳምንት መገባደጃ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !

ወልቂጤ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በደረጃ ሰንጠረዡ በሦስት ነጥብ ተበላልጠው የተቀመጡትን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ይሆናል።

ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥቦች አንዱን ብቻ አሳክተው በዘጠኝ ነጥቦች ወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ከአምስት ሣምንታት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ሀዋሳ ከተማን ይገጥማሉ። ወልቂጤዎች ሀምበርቾ ላይ የአንድ ለባዶ ድል ካስመዘገቡ በኋላ በተከታታይ ድል አላስመዘገቡም። ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶቹ በተጨማሪ ከፍተኛ የግብ ማስቆጠር ችግር ይታይበታል። በሊጉ ባደረጓቸው አስራ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ብቻ በማስቆጠር ዝቅተኛ የግብ መጠን ካስመዘገቡ ክለቦች በቅድሚያ ተቀምጠዋል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ኳስና መረብ ማገናኘቱም  ወቅታዊው የግብ ማስቆጠር ችግሩ ሌላው ማሳያ ነው። ይህንን በቡድኑ ውስጥ የሚታየው የግብ ማስቆጠር ችግር የመፍታትና የማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ለውጦች የማድረግ የቤት ሥራ የሚጠብቀው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች ስድስት ሽንፈትና አንድ ድል ካሳካው ሀዋሳ ከተማ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ድል ከቀናው ከወራጅ ቀጠናው የሚወጣበት ዕድል በእጁ አለ።


ከተከታታይ አምስት ሽንፈቶች በኋላ ወላይታ ድቻን አሸንፈው ነጥባቸውን አስራ ሁለት ማድረስ ችለው የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በመጨረሻው ሣምንት በአዳማ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት አገግመው ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ወልቂጤ ከተማን ይገጥማሉ። ሀዋሳዎች በማጥቃቱ ረገድ በጥሩ ጎኑ የሚነሳ በጎ ለውጦች በማድረግ የማጥቃት ክፍላቸው ማሻሻል ቢችሉም የተከላካይ ክፍላቸውን ማስተካከል ግን ቀላል አልሆነላቸውም።  የተከላካይ ክፍሉ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ላይ አስራ ስድስት ግቦችን ማስተናገዱም የመከላከል አደረጃጀቱ ክፍተት ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በሊጉ በጨዋታ በአማካይ 1.5 ግቦች በማስተናገድ መጥፎ የመከላከል ቁጥሮች ያስመዘገበውን የቡድኑ ዋነኛ ድክመት ማሻሻል ቀዳሚ ሥራቸው መሆን ይኖርበታል። ከዛ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረገውን ዓሊ ሱሌይማን ላይ መሰረት ያደረገውን የማጥቃት አጨዋወት ማጎልበት ሌላው የቤት ሥራቸው ነው።

በወልቂጤ ከተማ በኩል ወንድማገኝ ማዕረግ እና አሜ መሐመድ ከጉዳት ቢመለሱም የተወሰኑ ተጫዋቾች በደመወዝ ምክንያት ላይኖሩ እንደሚችሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ከቡድኑ ጋር ከሌሉት ሙጂብ ቃሲምና ሚሊዮን ሰለሞን ውጭ ጨዋታው የሚያመልጠው ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ቡድኖች 6 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ በሦስት ድል ቀዳሚ ሲሆን ወልቂጤ አንድ አሸንፎ በሁለት ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ ከተማ 8 ፤ ወልቂጤ ከተማ 6 ግቦች አስቆጥረዋል።

ጨዋታውን ለመምራት ሃይማኖት አዳነ በመሐል ዳኝነት ወጋየሁ አየለ እና ሶርሳ ዱጉማ በረዳትነት ተፈሪ አለባቸው በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይሟል።

ፋሲል ከነማ ከ ሻሸመኔ ከተማ

ከሁለት ጨዋታዎች ቆይታ በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ የሚገቡት ፋሲል ከነማዎችና አምስት ሽንፈት አልባ ሣምንታትን ያሳለፉት ሻሸመኔ ከተማዎች የሚያገናኘው ጨዋታ የሣምንቱ ማሳረጊያ ነው።

ከተከታታይ ሁለት ድሎች በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ስድስት ነጥቦች አንዱ ብቻ ያሳኩት ፋሲል ከነማዎች ዳግም ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ሻሸመኔን ይገጥማሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥልቀት ከሚከላከሉ ቡድኖች ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች በጥራት ሆነ በቁጥር ላቅ ያሉ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የተቸገሩት ዐፄዎቹ በመጨረሻው ሣምንትም ከመቻል ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ  የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ዕድሎች በመፍጠር ይሁን የተገኙትን ውስን ዕድሎች የመጠቀም ውስንነቶች ነበሯቸው።
በነገው ዕለትም በተመሳሳይ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ ሦስት ግቦች ብቻ ያስተናገደ እና ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት ያለው ሻሸመኔ ከተማን እንደመግጠማቸው መሰል ፈተናዎች ማስተናገዳቸው አይቀሬ ነው። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በውድድር ዓመቱ በውጤት ረገድ የሚታይባቸውን የወጥነት ችግር ለመቅረፍ የፊት መስመራቸው ውጤታማነት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን ሦስት ለባዶ ካሸነፈበት ሳምንት በኋላ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩም የቡድኑ የፊት መስመር መዳከም ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታም ወደ ራሱ የግብ ክልል ተጠግቶ ለመጫወት የሚመርጥ ጠጣሩን የሻሸመኔ የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት የሚያስችል የቅብብሎች ትዕግስት እና የግብ ምንጭ አማራጮች ማስፋት ይጠበቅባቸዋል።


ላለፉት አምስት ሣምንታት ሽንፈት አልባ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኙ ሻሸመኔ ከተማዎች ምንም እንኳ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ባይችሉም በጥሩ መነቃቃት ይገኛሉ። ሻሸመኔዎች የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ አጨዋወታቸውን በመቀየር ጠጣርና መከላከል ላይ ያመዘነ አቀራረብ በመምረጥ ቢያንስ ከተከታታይ ሽንፈቶች ርቀዋል። የአሰልጣኝ ዘማርያም አቀራረብ የቡድን ሚዛን ላይ ክፍተቶች ይስተዋልበታል። አቀራረቡ በአመዛኙ መከላከል ላይ ያዘነበለ መሆኑን ተከትሎ ቡድኑ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል አናሳ የተጫዋቾች ቁጥር እንዲኖረው አስችሎታል። ይህንን ተከትሎ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል። አሰልጣኝ ዘማርያም በነገው ዕለትም በተመሳሳይ መከላከል ላይ ያተኮረ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል። ቡድኑ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል የሚስተዋልበትን ውስንነት ለመቅረፍም በፈጣን የመልሶ ማጥቃትና በረዣዥም ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል።

በፋሲል ከነማ በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ፍቃዱ ዓለሙ ልምምድ ቢጀምሩም ለነገው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። በሻሸመኔ ከተማ በኩል ቻላቸው መንበሩ በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም። ከዛ በተጨማሪ አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ በቅጣት ጨዋታውን አይመሩም።

በሊጉ ከ16 ዓመታት በኋላ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በሚሊኒየሙ ባደረጉት ብቸኛ ጨዋታ ፋሲል ከነማ 2ለ1 አሸንፏል።

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት አዳነ ወርቁ ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ደስታ ጉራቻ ረዳቶች መለሠ ንጉሤ በአንፃሩ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድቧል።