ሪፖርት | የ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሸንፏል

በሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ማጣርያ የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካን 3ለ0 ረታለች።

የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ማጣርያ የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ሲደረግ በመጀመሪያው አጋማሽ በራውዳ ዓሊ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ፍጹም የበላይነት በመውሰድ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ የተጋጣሚን የግብ ሳጥን መፈተን ችሏል።

በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በማድረግ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያውያን 10ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሳባ ኃ/ሚካኤል በቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ሳትቆጣጠረው ቀርታ የተመለሰውን ኳስ ያገኘችው ማንዐየሽ ተስፋዬ መረቡ ላይ አሳርፋዋለች።


ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በተሻለ ግለት ተጨማሪ ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት ትናንሾቹ ሉሲዎች 19ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ማሕሌት ምትኩ የሰነጠቀችውን ኳስ በፍጥነት ሾልካ በመውጣት የተቆጣጠረችው ህዳት ካሱ በግሩም አጨራረስ ስሟን ከግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ማካተት ችላለች።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል የአሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ ተጫዋቾች በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ማረጋጋት ሲችሉ 50ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሜላት ጌታቸው እና ማሕሌት ምትኩ የፈጠሩትን ንጹህ የግብ ዕድል የደቡብ አፍሪካ ተከላካዮች ከመስመር አግደውታል።

በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል እጅግ በተቸገሩት የደቡብ አፍሪካ እንስቶች በኩል አድሬልፍ ማሊሎሆኖሎ እየገፋች በወሰደችው ኳስ ከሳጥን አጠገብ ያደረገችው እና ግብ ጠባቂዋ የያዘችው ኳስ የተሻለ ተጠቃሽ እንቅስቃሴያቸው ነበር።

በኢትዮጵያ በኩል የጨዋታው ኮከብ የነበረችው ህዳት ካሱ ከሜላት ጌታቸው የተቀበለችውን ኳስ በሳጥኑ የግራ ጠርዝ ይዛው በመግባት እጅግ አስደናቂ በሆነ አጨራረስ ከመረብ አሳርፋው ለራሷ ሁለተኛ ለብሔራዊ ቡድኗ ሦስተኛ ግቧን ስታስመዘግብ በቀሪ ደቂቃዎችም ሜላት ጌታቸው እና ሳባ ኃ/ሚካኤል ከጨዋታ እና ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ሆኖም ጨዋታው በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።