የመቻሉ ወሳኝ ተጫዋቾች ለምን ያህል ጊዜ ከጨዋታ ይርቃል?

በዘንድሮ የመቻል አስደናቂ ግስጋሴ ውስጥ ቁልፍ ሚናን እየተወጣ የሚገኘው ከነዓን ማርክነህ የጉዳት መጠን ታውቋል።

መቻል በአስራ ሦስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር ሲዳማ ቡናን ሁለት ለአንድ በመርታት የሊጉን መሪነት በተረከበበት ጨዋታ የመስመር አጥቂው ከነዓን ማርክነህ የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ጉልበቱ ላይ ከበድ ያለ ህመም አስተናግዶ ተቀይሮ መውጣቱ ይታወሳል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከዲኤስቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ የከነዓን ህመም ከበድ ያለ ሊሆን እንደሚችል እና በእግሩ መራመድ አቅቶት እንደነበረ ገልፀው ምን አልባትም ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ ስጋታቸውን መግለፃቸው ይታወሳል። አያይዘውም
የተጫዋቹ መጎዳት በቡድናቸውም ላይ ተፅዕኖ ቢፈጥርም በሌሎች ተጫዋቾች ቀሪ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር።

ነገርግን በዛሬው ዕለት በጦር ኃይሎች ሆስፒታል የህክምና ምርመራውን ያደረገው ከነዓን የጉልበቱ የኋለኛው ክፍል ላይ ህመሙ እንዳጋጠመው የተገለፀ ሲሆን የህክምናው ውጤት እንደሚያሳየው ከሆነ ህመሙ የተፈራውን ያህል ከባድ እንዳልሆነ እና ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚያደርጉት የሊግ ጨዋታ ብቻ የሚያመልጠው ሲሆን በ15ኛ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ሻሸመኔን ሲገጥም ደግም ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በ11 የሊግ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎን ያደረገው ከነዓን ለቡድኑ አራት ግቦችን በማስቆጠር ወሳኝነቱን እያሳየ የሚገኝ ሲሆን የጉዳቱ መጠን በተፈራው ልክ አለመሆኑ መቻል በሰንጠረዡ አናት ለሚያደርገው ፉክክር እንደሚያግዘው ይጠበቃል።