ሪፖርት | በአራት ደቂቃ ውስጥ በተቆጠሩ ጎሎች ሻሸመኔ እና ድሬዳዋ አቻ ወጥተዋል

የምሽቱ የሻሸመኔ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩ ግቦች በ1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሻሸመኔ ከተማ በፋሲል 2ለ0 ከተረቱበት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ያደረጉ ሲሆን ቅጣት ባስተናገደው ወጋየሁ ቡርቃ ምትክ ያሬድ ዳዊትን ፣ ሔኖክ ድልቢን በጌትነት ተስፋዬ ሲተኩ ድሬዳዋ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕናው የአቻ ውጤት አንፃር ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ አቤል አሰበን በያሬድ ታደሰ በብቸኝነት ቀይረዋል።

በወጣቱ የመሐል ዳኛ ሀይማኖት አዳነ መሪነት በጀመረው ጨዋታ ፈጣን የግብ ሙከራን ያስመለከተን ገና በጊዜ 2ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ሻሸመኔዎች ግብ ጠባቂው ኬኒ ሰይዲ ከራሱ ግብ ክልል በረጅሙ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ የለጋውን ኳስ በግራ አብዱልቃድር ተቆጣጥሮ ነፃ ሆኖ ለተገኘው አለን ካይዋ ሰጥቶት አጥቂውም ከፍ በማድረግ አስቆጥራለው ያላትን ኳስ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሣዬ በቀላሉ ተቆጣጥሮበታል። ድሬዳዋ ከተማዎች ከአንድ ደቂቃ መልስ ሱራፌል ጌታቸው ከቀኝ የግቡ ቦታ በቀጥታ ወደ ጎል መቶ ግብ ጠባቂው ኬኒ ሰይዲ በጥሩ ቅልጥፍና ባዳነበት አጋጣሚ ቅፅበታዊ ምላሽን ሰንዝረዋል ። ሻሸመኔዎች በረጃጅሙ ከተከላካይ ጀርባ ማረፊያቸውን በሚያደርጉ ኳሶች አጥቂው አለን ካይዋን የጥቃት መነሻ አድርገው ቢጫወቱም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ደርሰው ልዩነት በመፍጠሩ ረገድ ግን በእጅጉ ደካሞች ሆነው ታይተዋል።

 

የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወስደው ወደ ግራ በማጋደል በይበልጥ መንቀሳቀስን የመረጡት ድሬዳዋ ከተማዎች የጥራት ጎዶሎነት ይኑራቸው እንጂ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ በተወሰነ መልኩ ሻል ብለው ታይተዋል። 11ኛው ደቂቃ ሔኖክ አንጃው ከማዕዘን አሻምቶ መሐመድ አብዱልጋኒዮ በግንባር ገጭቶ ዳግም ኳሷ ስትመለስ ኤፍሬም በግንባር ገጭቶ የግቡን ቋሚ ብረት ገጭታ ኳሷ ተመልሳበታለች። በሌላ የድሬዳዋ ሙከራ 22ኛው ደቂቃ ላይም ከቅጣት ምት ዳግማዊ አባይ በቀጥታ ወደ ግብ መቶ ኬኒ ሰይድ ሳይቸገር ይዞበታል። ሜዳ ላይ ከሚታዩ ብክነት ከበዛባቸው ቅብብሎች እና የጎል ዕድሎችም እምብዛም ሲፈጠሩ ያላስተዋልንበት ቀጣዩ የሁለቱ ቡድኖች የጨዋታ ደቂቃ ከፉክክር አኳያ ወረድ ባለ ይዘት ውስጥ ሆኖ ከቀጠለ በኋላ ያለ ጎል አጋማሹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ጨዋታው ከዕረፍት እንደተመለሰ 50ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ተመልክተናል። ኤፍሬም አሻሞ የሻሸመኔ ተጫዋች የሆኑትን ያሬድ እና ምንተስኖትን ጫና ውስጥ በመክተት የነጠቀውን ወደ ግራ ልኮለት አብዱለጢፍ መሬት ለመሬት ሲያሻማ ግብ ጠባቂው ኬኒ ኳሷን ጨርፏት ከጀርባው የነበረው ሱራፌል ጌታቸው ወደ ግብነት ለውጧት ድሬዳዋን መሪ ማድረግ ቢችልም ከደቂቃዎች መልስ በተቃራኒው ሻሸመኔዎች የአቻነት ግብ አግኝተዋል። 54ኛው ደቂቃ ጌትነት ተስፋዬ በተከላካዮች መሐል የተላከለትን ሰንጣቂ ኳስ ለመጠቀም ጥረት ሲያደርግ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ በሳጥን ውስጥ ጥፋትን በተጫዋቹ ላይ በመስራቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አለን ካይዋ ከመረብ አገናኝቶት ጨዋታው ወደ 1ለ1 ተሸጋግሯል።

ሽግግር ላይ ባተኮረ መንገድ ተንጠልጣይ ኳሶችን መጠቀም ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች ባደረጉበት ሰዓት ተጫዋች በቀይ አጥተዋል። 57ኛው ደቂቃ ኤልያስ አህመድ ሀብታሙ ንጉሴ ኳስን ሊያስጥለው ጥረት በሚያደርግበት ወቅት በክርኑ በመማታቱ የዕለቱ ዳኛ ሀይማኖት አዳነ በቀጥታ ቀይ ካርድ ተጫዋቹን ከሜዳ አስወግደውታል። አንድ ተጫዋችን በቀይ በማጣታቸው አጥቂው ኤፍሬምን በቴዎድሮስ ሀሙ በመተካት መከላከል ላይ ሚዛናዊ ለመሆን ድሬዳዋ ከተማዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ሞክረዋል። የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ቢኖራቸውም መረጋጋት የማይታይባቸው ሻሸመኔዎች በመስመር በኩል በጥልቀት ዕድሎችን ፈጥረው የነበረ ቢሆን የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው የተሳኩ አልነበሩም።

58ኛው ደቂቃ አለን ለአሸናፊ ሰጥቶት ከቀኝ ወደ ውስጥ ተጫዋቹ ያሳለፈውን አብዱልቃድር በቀላሉ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ አብዩ አስጥሎታል። 72ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሞ በተለጋ ኳስ ሱራፌል ድንገተኛ ሙከራን አድርጎ ግብ ጠባቂው ኬኒ ካወጣበት አጋጣሚ በስተቀር በተጋጣሚያቸው ጫና ሲፈጠርባቸው የነበሩት ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻም ተሳክቶላቸው ጨዋታው በ1ለ ውጤት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው በኋላ የድሬዳዋ ከተማው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ ጥሩ አጀማመር ብናደርግም በኋላ ላይ ማፈግፈጎች በመጀመሪያው አጋማሽ እንደነበሩ ከዕረፍት መልስ ግን ጎል ቢያስቆጥሩም ተጫዋች በቀይ ካርድ ማጣታቸው ጫና እንደተፈጠረባቸው እና ያም ሆኖ ዕድሎችን ፈጥረው መጠቀም እንዳልቻሉም ጭምር ተናግረዋል። የሻሸመኔ ከተማው ረዳት አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ በበኩላቸው ጥሩ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድን በኩል መደረጉን ተናግረው አስበው የመጡት ሦስት ነጥብ ቢሆንም አለመሳካቱ እና ተጋጣሚያቸው ጎዶሎ ሆኖ የተገኘውን ዕድልም ጭምር አለመጠቀማቸው እንዳስቆጫቸውም ተናግረዋል።