የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ15ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በመመርኮዝ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አሰላለፍ 4-1-2-3

ግብ ጠባቂ

አብዩ ካሳየ – ድሬዳዋ ከተማ

ወጣቱ ግብጠባቂ ረዘም ያሉ ሳምንታትን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ቢያሳልፍም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያገኘ የሚገኘውን የመጫወት ዕድል ግን ራሱን ለማሳየት በሚገባ እየተጠቀመበት ይገኛል። ብርቱካናማዎቹ ሠራተኞቹን በቻርለስ ሙሴጌ ብቸኛ ግብ 1ለ0 ሲያሸንፉ የግብ ጠባቂያቸው አብዩ ካሳየ የነቃ ተሳትፎ ላሳኩት ውጤት ወሳኝ ነበር። በጨዋታው ወጣቱ የግብ ዘብ በተለይ በሁለት አጋጣሚዎች ያመከናቸው ኳሶች በጠባብ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ እጅግ ወሳኝ ነበሩ።

ተከላካይ

መሳይ አገኘሁ – ባህር ዳር ከተማ

ባህር ዳር ከተማን ከስድስት ተከታታይ ሳምንት ውጤት አልባ ጉዞ በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ሁሉም ተጫዋቾች ያሳዩት ተጋድሎ ለውጤቱ መሳካት ትልቁን ድርሻ ቢወስድም በቀኝ መስመር በጨዋታ ሳምንቱ ከተመለከተናቸው ተጫዋቾች ከዳግማዊ ዓባይ ጋር የተፎካከረው መሳይ ለቸርነት ግብ ኳሷን አመቻችቶ በማቀበሉ እንዲሁም በቦታው ከነበረው የተሻለ አፈፃፀም መነሻነት የተሻለ ነው በሚል ምርጫችን ሆኗል።

አማኑኤል ተርፉ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ወጣቱ ተከላካይ በፈረሰኞቹ ቤት ከታዳጊ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ካደገበት ጊዜ አንስቶ የሚታይ እድገትን እያሳየ ሲገኝ ዘንድሮ ደግሞ በተለይ በራስ መተማመኑ በኩል ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ ይገኛል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በአጋማሹ የመጨረሻ ጨዋታው ሲዳማ ቡናን አንድ ለምንም ሲረታ አማኑኤል ተርፉ በመከላከሉ በኩል ካሳየው ድንቅ ብቃት በተጨማሪ የማሸነፊያውን ወሳኝ ጎል በማስቆጠር የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ጎሉን በማግኘቱ ያለ ተቀናቃኝ በስብስባችን ውስጥ እንዲካተት ሆኗል።

እስማኤል አብዱልጋኒዩ – ድሬዳዋ ከተማ

በአጋማሹ የውድድር ዘመን ከታዩ ምርጥ ተከላካዮች መካከል ጋናዊው የኋላ ደጀን እስማኤል አብዱልጋኒዩ አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ድሬዳዋ ራሱን ከወራጅ ቀጠና ለማራቅ ወሳኝ ፍልሚያ ከወልቂጤ ከተማ ጋር አድርጎ በድል ባጠናቀቀበት ጨዋታ እስማኤል የመከላከል ድርሻውን በአግባቡ ከመወጣቱ ባሻገር ላስቆጠሩት ግብ ቁልፍ መነሻ የነበረ ሲሆን በሌላ አጋጣሚም ቡድኑ ከእርሱ ጎል ለማግኘት ተቃርቦ በግቡ ቋሚ የተመለሰበት ሂደት ሲታይ በቦታው ከያሬድ ባየህ ጋር ተፎካክሮ ቀዳሚ ተመራጫችን ሆኗል።

ረመዳን የሱፍ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ግራ መስመር ላይ ብዙም አሳማኝ እንቅስቃሴ ያደረጉ ተከላካዮች ማግኘት አዳጋች በሆነበት በዚህ ሳምንት የፈረሰኞቹ የግራ መስመር ተጫዋች ረመዳን የሱፍ በአንጻራዊነት የተሻለ አፈፃፀም አሳይቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ባደረገው የሲዳማ ቡናው ጨዋታ ረመዳን ከተለምዷዊ ቦታው በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የቦታ ሽግሽግ በማድረግ ወደ መስመር አጥቂነት በመቀየር በሁለቱም ሚና ቡድኑ ውጤት ይዞ እንዲወጣ ባደረገው እንቅስቃሴ በምርጥ አስራ አንድ ውስጥ መግባት ችሏል።

አማካይ

መለሰ ሚሻሞ – ሀዲያ ሆሳዕና

ከተጠባባቂ ወንበር በመነሳት የሚያገኙትን ዕድሎች በአግባቡ እየተጠቀሙ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መለሰ ሚሻሞ ነው። ከሀዋሳ ከተማ ጋር 1ለ1 ተለያይተው በግማሽ የውድድር ዘመኑ አሥረኛ የአቻ ውጤታቸውን ሲያስመዘግቡ የአማካዩ ታታሪነት በጉልህ የሚነሳ ነበር። በተለይም ቡድኑ ጨዋታውን መምራት እንዲችል እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ተገልብጦ ማራኪ ግብ ማስቆጠር የቻለው መለሰ ከግቡ ባሻገር ያደረገው እንቅስቃሴ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ ለመካተት አስችሎታል።

ከነዓን ማርክነህ – መቻል

ቁመታሙ ተጫዋች ከነዓን ማርክነህ በየጨዋታዎቹ ለመቻሎች እየሰጠ ያለው አገልግሎት ከፍ እያለ መጥቷል። መቻሎች ሻሸመኔ ከተማን 1ለ0 አሸንፈው የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት ሲያጠናቅቁ የቡድኑን ግብ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር የቻለው ከነዓን በተደጋጋሚ ይፈጥራቸው የነበሩት የግብ ዕድሎች እና ያደረገው ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያለ ተቀናቃኝ በቦታው ተመራጭ አድርጎታል።

ሽመልስ በቀለ – መቻል

መቻል በዘንድሮ ዓመት ላሳየው ከፍተኛ መሻሻል የአንበሳውን ድርሻ ከሚወስዱ ተጫዋቾች መካከል የአማካዩ ሽመልስ በቀለ ድርሻ በጉልህ የሚታይ ነበር። እንደ ቡድን አጋሩ ከነዓን ሁሉ የተሳካ የጨዋታ ቀን ያሳለፈው ባለ ብዙ ልምዱ ሽመልስ የተጋጣሚን ሳጥን በተደጋጋሚ መፈተን ሲችል ከነዓን ላስቆጠራት ግብም መነሻ የነበረ በመሆኑ በቦታው ያደረገው ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ በቦታው ተመራጭ እንዲሆን አስችሎታል።

አጥቂ

አዲስ ግደይ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በሲዳማ ቡና ድንቅ የውድድር ዓመታቶችን ካሳለፈ በኋላ የጉልበት ጉዳት የእግርኳስ ዕድገቱን ፈትኖት የቆየው አዲስ ግደይ ዘንድሮ ዳግም የተወለደ ይመስላል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስቶ ፋሲል ከነማን በረታበት ጨዋታ የቡድኑን የመጀመሪያ እና ወደ ጨዋታ የሚመልስ ግብ በአስደናቂ ሁኔታ ከቅጣት ምት ማስቆጠር የቻለው አዲስ ከግቡ ባሻገር ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረገው አስተዋጽኦም ከፍ ያለ ነበር።

ቢኒያም ዓይተን – አዳማ ከተማ

የሜዳ ላይ ተፅእኖው በየጨዋታዎቹ ከፍ እያለ የመጣው ወጣቱ አጥቂ ቢኒያም ዓይተን አዳማዎች በመቀመጫ ከተማቸው ባደረጉት የመጨረሻ ጨዋታ ከኢትዮጵያ መድን ጋር በሁለት ግብ ልዩነት ሲመሩ ቆይተው የኋላ ኋላ በተቆጠሩባቸው ሁለት ግቦች አቻ ሲለያዩ የቡድኑን ሁለቱንም ግቦች ያስቆጠረው ቢኒያም ቡድኑን አሸናፊ ለማድረግ በግሉ የተወጣው ሚና የላቀ ነበር።

ያሬድ ዳርዛ – ኢትዮጵያ መድን

ኢትዮጵያ መድን በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ቢገኝም ያሬድ ዳርዛ ሜዳ ውስጥ የሚቻለውን ለማድረግ እየተጋ ይገኛል።መድኖች በሁለት ግብ ከመመራት ተነስተው ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋሩ የመስመር አጥቂው ብቃት የሚደነቅ ነበር። ያሬድ ለመጀመሪያው የብሩክ ሙሉጌታ ግብ መነሻ የነበር ሲሆን ሁለተኛውን ግብም በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር መቻሉ በቦታው ተመራጭ እንዲሆን አስችሎታል።

ተጠባባቂዎች

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን
ያሬድ ባየህ – ባህር ዳር ከተማ
በረከት ሳሙኤል – ሀዋሳ ከተማ
በፍቃዱ ዓለማየሁ – ኢትዮጵያ ቡና
ዳግማዊ ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ
ጋቶች ፓኖም – ፋሲል ከነማ
ሱራፌል ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ
ወገኔ ገዛኸኝ – ኢትዮጵያ መድን
ቸርነት ጉግሳ – ባህር ዳር ከተማ
ቻርለስ ሙሴጌ – ድሬዳዋ ከተማ

አሰልጣኝ – በጸሎት ልዑልሰገድ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስተው ፋሲል ከነማን 4ለ2 ሲያሸንፉ አሰልጣኙ በጸሎት በተለይም ከዕረፍት መልስ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን የግብ ዕድል የመፍጠር አቅም በመግታቱ በኩል እጅግ ስኬታማ አቀራረብ የነበራቸው ሲሆን ጠንካራው የዐፄዎቹ የተከላካይ መስመር ላይ አራት ግቦችን በማስቆጠር ማሸነፍ መቻላቸው የሳምንቱን ምርጥ ቡድናችንን እንዲመሩ አስችሏቸዋል።