የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች

የአራተኛ ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ነገ በሚደረግ አንድ ጨዋታ ይጀመራል፤ የሩብ ፍፃሜው የመክፈቻ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

ከቀናት በፊት አራት ግቦች ባስመለከተን ጨዋታ ነጥብ ተጋርተው የወጡትን ክለቦች የሚያገናኝ የአራተኛው ዙር የመክፈቻ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች


በሀያ ሦስት ነጥቦች 6ኛ ደረጃን ይዘው የመጀመርያውን ዙር የሊጉ ውድድር ያገባደዱት አዳማ ከተማዎች ከስድስት ሽንፈት አልባ የሊግ ጨዋታዎች መልስ በኢትዮጵያ ዋንጫ ያላቸውን ጉዞ ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ። በሁለተኛው ዙር ሙሴ ኪሮስ፣ መስዑድ መሐመድ፣ ነቢል ኑሪና መሐሪ መና በራሱ ላይ ባስቆጠራት ግብ አማካኝነት ሲዳማ ቡናን በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ውድድሩን የጀመሩት አዳማዎች በሦስተኛው ዙር በአሸናፊ ኤልያስና የቦና ዐሊ ሁለት ግቦች ታግዘው ቢሾፍቱ ከተማን በማሸነፍ ነበር ወደ ሩብ ፍፃሜው የተሻገሩት። በነገው ዕለትም ከቀናት በፊት ከኋላ ተነስቶ ነጥብ ከተጋራቸው ኢትዮጵያ መድን ጋር ጠንካራ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።


በመጀመርያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች አስራ ሁለት ነጥብ ሰብስበው በ13ኛ ደረጃነት የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች በኢትዮጵያ ዋንጫ ግን ጥሩ ጉዞ እያደረጉ ይገኛሉ። በነገው ዕለትም ባለፈው የውድድር ዓመት ዕውን ያላደረጉትን በአህጉራዊ ውድድሮች የመሳተፍ ህልም ለማሳካት አዳማ ከተማን ይገጥማሉ። ኢትዮጵያ መድኖች በሁለተኛው ዙር በችኩሜካ ጎድሰንና ያሬድ ዳርዛ ግቦች ታግዘው ድሬዳዋ ከተማን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ እንዲሁም በሦስተኛው ዙር በችኩሜካ ጎድሰንና በርናንድ ኦቼንግ ግቦች ታግዘው አርሲ ነገሌን በተመሳሳይ ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ነው ወደዚ ዙር የበቁት። በነገው ዕለትም በውድድሩ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ካስቆጠረላቸው አጥቂ ውጭ ወደ ሜዳ ይገባሉ።