የአቡበከር ናስር አሁናዊ ሁኔታ

አሰልጣኝ ሩላኒ ማክዌና በአቡበከር ናስር ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ዙርያ አስተያየት ሰጥተዋል።

ከሳምንታት በፊት የደቡብ አፍሪካው ክለብ ተጨማሪ የውጭ ዜግነት ያለው ተጫዋች ማስፈረሙን ተከትሎ የአቡበከር ናስር ቆይታ ጥያቄ ምልክት ውስጥ መግባቱ ይታወሳል። አሁን ደግሞ አሰልጣኝ ሩላኒ ሞክዌና ስለ ተጫዋቹ አሁናዊ ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት የተጫዋቹ ቆይታ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቷል። ለእግር ኳስ ሂወቱ አደጋ የሆነ ጉዳት እንዳጋጠመው የገለፁት አሰልጣኙ ክለቡ ይፋዊ መግለጫ ይሰጥበታል ብለው እንደሚያስቡም ተናግረዋል።

” ክለቡ መግለጫ ይሰጣል ብዬ አስባለሁ፤ ነገር ግን ከፓይሬትስ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ያጋጠመው በጣም ከባድ እና የተወሳሰበ ጉዳት ነው። “ገና አላገገመም ግን ለማገገም በጣም እየታገለ ነው። ይህም ትንሽ አሳዛኝ ነው፤ ምክንያቱም ይህ አይነት ሁኔታ ለእግር ኳስ ሂወቱ የሚያሰጋ ነው” ብለዋል። አሰልጣኙ አክለውም ተጫዋቹ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውና በቅርቡ ይመለሳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። “እኛ ልንሰጠው የምንችለውን ሁሉ ድጋፍ ያስፈልገዋል፤ በርግጥ ተጫዋቾቹን የሚንከባከብ ጥሩ ክለብ ውስጥ ነው ያለው። በቅርቡ እናየዋለን ብለንም ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ወደ ደቡብ አፍሪካው ክለብ ከመራ በኋላ የቁርጭምጭሚትና የጉልበት ጉዳት ጨምሮ ሦስት ከባባድ ጉዳቶች የገጠሙት ይህ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በቀጣይ ጊዜያት ከክለቡ ጋር ያለውን ቆይታ ይወሰናል ተብሎ ይገመታል።