ቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች አስፈረመ

አቤል ያለውን ወደ ግብፅ የሸኙት ፈረሰኞቹ በከፍተኛ ሊጉ ክለብ የግማሽ ዓመት ቆይታ ያደረገው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ማስፈረማቸውን ይፋ አድርገዋል።

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ላይ በ28 ነጥቦች በመቀመጥ ያገባደደው ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ተጫዋች ታምራት ኢያሱ ነው።

ከአርባ ምንጭ ከተማ ከተገኘ በኋላ በኦሜድላ ቆይታን በማድረግ በያዝነው ዓመት ወደ ነጌሌ አርሲ የተቀላቀለው ታምራት በምድብ ለ ተሳታፊው ነጌሌ አርሲ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን በሊጉ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ በድምሩ 9 ጎሎችን ማስቆጠርም ችሏል። አሁን ደግሞ የዝውውር መስኮቱ መከፈቱን ተከትሎ ፈረሰኞቹን ተቀላቅሏል።

ክለቡ በዛሬው ዕለት በይፋ የግብፁን ዜድ ክለብ የተቀላቀለው አቤል ያለውን ቦታ በሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር በታምራት እንደሚሸፍን ይጠበቃል።