ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ሁለተኛውን ዙር በድል ጀምረዋል

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልቂጤ ከተማን 2ለ0 ረቷል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲገናኙ ሠራተኞቹ በ15ኛው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ 1ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ተመስገን በጅሮንድ ፣ መድን ተክሉ ፣ ዳንኤል ደምሱ ፣ ጌቱ ኃይለማርያም እና ፉዓድ አብደላ በዳንኤል መቅጫ ፣ መሳይ ጳውሎስ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ አቡበከር ሳኒ እና ራምኬል ሎክ ተተክተው ሲገቡ ፈረሰኞቹ በተመሳሳይ ሳምንት ሲዳማ ቡናን 1ለ0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ዳዊት ተፈራ እና ከነገሌ አርሲ ፈርሞ የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታውን የሚያደርገው ታምራት ኢያሱ በተገኑ ተሾመ እና ሞሰስ ኦዶ ተተክተው ገብተዋል።

10፡00 ሲል 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አስመልክቶ ጀግኖችን በመዘከር በዋና ዳኛ ዓባይነህ ሙላት መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያወቹ 20 ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝረዋል። በተለይም 14ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ታምራት ኢያሱ ከቢኒያም በላይ በተመቻቸለት ኳስ ከሳጥን አጠገብ ንጹህ የግብ ዕድል ቢያገኝም በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ መልሶበታል።

መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ በቁጥር በመብዛት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባቱ በኩል የተሻሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ 18ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው ሄኖክ አዱኛ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ያስገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ተከላካዩ ተስፋየ መላኩ ከመለሰበት በኋላ ያገኘው ዳግማዊ አርዓያ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አስወጥቶበታል።

ቀስ በቀስ በኳስ ቁጥጥሩ የተወሰደባቸውን ብልጫ በመጠኑ ያስመልሱ እንጂ ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት የተቸገሩት ወልቂጤ ከተማዎች በሙሉዓለም መስፍን እና በተመስገን በጅሮንድ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ግብ ጠባቂውን ባሕሩ ነጋሽን መፈተን አልቻሉም። በአንጻሩ ጊዮርጊሶች በረመዳን የሱፍ አማካኝነት ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ ጊዮርጊሶች ከቢኒያም በላይ በሚሰነጠቁ ኳሶች በርካታ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙባቸው ሲቀሩ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ግን በረከት ወልዴ እና አማኑኤል ተርፉ የተሻሉ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ያሳለፉት ሠራተኞቹም ተሳክቶላቸው ግብ ሳያስተናግዱ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወልቂጤ ከተማዎች በተሻለ ግለት መንቀሳቀስ ቢችሉም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ አማኑኤል ኤርቦ እና ሞሰስ ኦዶን በታምራት ኢያሱ እና ዳግማዊ አርዓያ ቀይረው በማስገባት ውጤታማ ሆነዋል። በዚህም 62ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ በግራ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አማኑኤል ኤርቦ በግንባር ሲጨርፈው ኳሱ የወልቂጤውን የመስመር ተከላካይ ሄኖክ ኢሳይያስ ትከሻ ገጭቶ መረቡ ላይ አርፏል።

ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጋጣሚያቸውን ለመፈተን የተቸገሩት የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት ተጫዋቾች ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ 64ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ጋዲሳ መብራቴ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሙሉዓለም መስፍን በግንባር በመግጨት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበታል።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ያስቀጠሉት ጊዮርጊሶች 73ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ሄኖክ አዱኛ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ያገኘው በረከት ወልዴ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ በጥሩ ብቃት መልሶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም መጠነኛ ፉክክር ተደርጎ 89ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከአማኑኤል ኤርቦ በተመቻቸለት ኳስ ካደረገው ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ስድስት ደቂቃዎች ውስጥ አምስተኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አላዛር ሳሙኤል በቀኝ መስመር ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ረመዳን የሱፍ ዓየር ላይ እንዳለ በእግሩ በመምታት አስቆጥሮት ቅዱስ ጊዮርጊስን 2ለ0 በሆነ ውጤት ባለ ድል አድርጓል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት በራሳቸው ስህተት ግቦችን ማስተናገዳቸውን እና የግብ ዕድሎችን አለመጠቀማቸውን ሲገልጹ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበረ በመናገር በሁለተኛው አጋማሽ ግለታቸውን ጨምረው ግብ ማስቆጠራቸውን በመግለጽ ታምራት ኢያሱ ከቡድኑ ጋር ሲዋሃድ ጥሩ ነገር እንደሚጠብቁበት በመጠቆም አማኑኤል ኤርቦ ላይም ወደፊት ብዙ እንደሚጠብቁ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።