ተመስገን ዳና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሊመለስ ነው

ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከተለያየ በኋላ ያለ ኃላፊነት የቆየው ተመስገን ዳና ወደ ሊጉ ለመመለስ ከአንድ ክለብ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል።

የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር አገባዶ የሁለተኛው ዙር ፍልሚያ የጀመረ ሲሆን ክለቦችም በተጫዋች የዝውውር መስኮት ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። ከተጫዋቾች ዝውውር ጎን ለጎን ደግሞ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊጉን የተቀላቀልል ሀምበሪቾ በአጋማሹ አሠልጣኝ የሾመ የመጀመሪያው ክለብ ለመሆን ከጫፍ ደርሷል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የተቀመጠው ሀምበሪቾ ከአሠልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር ያለፉትን ሳምንታት ድርድር ሲያደርግ የሰነበተ ሲሆን በመጨረሻም መስማማት ላይ መደረሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በቀጣይ የወረቀት ስራዎች ከተጠናቀቁም ክለቡ በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ ሜዳ ተገኝተው እንደሚመሩ ይጠበቃል።