ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከድንቅ ብቃት ጋር ሲዳማ ቡናን ረቷል

ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩ ጎሎች ኢትዮጵያ ቡና ከጨዋታ ብልጫ ጋር ሲዳማ ቡናን 3ለ0 በመርታት የዓመቱ ስምንተኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን የ15ኛ ሳምንት መርሀግብር ከሀምበሪቾ ጋር ያለ ጎል ካጠናቀቀበት ጨዋታ ኪያር መሐመድን በአስራት ቱንጆ ብቻ ተክተው ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። መሐመድ ሙንታሪ ፣ ቡልቻ ሹራ ፣ ብርሃኑ በቀለ ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለን አስወጥተው በምትካቸው መክብብ ደገፉ ፣ መኳንንት ካሳ ፣ ደግፌ ዓለሙ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን እና ዳመነ ደምሴ ተቀይረው ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ፍፁም የበላይነት በታየበት ጨዋታ በመስመሮች ሆነ መሀል ለመሀል እድሎችን በመፍጠር የተሻሉ ነበሩ ፤ በ9ኛው መስፍን ታፈሰ በጥሩ ዕይታ ያቀበለውን ኳስ አንተነህ ወደ ጎል ቢመታም ደስታ ዮሐንስ በጥሩ ሽፋን ኳሷን ባወጣበት ኳስ ሙከራ ማድረጋቸውን የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች አብዱልከሪም ወርቁ ከርቀት ካደረጋት እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት እንዲሁም ሌሎች ተደጋጋሚ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም በአጋማሹ ቀዳሚ የሚያደርጋቸውን ጎል ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች የሚተዋቸውን ክፍተቶች በመጠቀም ረገድ በመጨረሻዎቹ ደቂቃ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ሁለት አደገኛ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም በበረከት አማረ እና በኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ጥረት ጎል ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በይበልጥ ግለቱ ከፍ ብሎ ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡና በአንድ ሁለት ቅብብል የመስመር አጨዋወታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ብልጫውን ወስደው ያለ መታከት የግብ ሙከራዎች ያደረጉበት ነበር።

በ49ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ሲዳማ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ መስፍን ታፈሰ ሞክሮ የግቡን ቋሚ ታካ ወደ ውጭ ስተወጣ በ53ኛው ደቂቃ እንዲሁ ከግራ መስመር በተነሳ ኳስ በፍቃዱ ዓለማየሁ ያደረገው ሙከራ የግቡ ቋሚ ብረት መልሶበታል።

ጎልን ለማስቆጠር የሲዳማ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ያነፈንፉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጥረታቸው ሰምሮ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብም በስተመጨረሻም አግኝተዋል። 64ኛው ደቂቃ በመስመር ሲያጠቁ አስፈሪ መልክ የሚታይባቸው ቡናማዎቹ አስራት ለአብዱልከሪም ወርቁ ሳጥን ውስጥ የሰጠውን ኳስ አማካዩ ወደ ጎል አክርሮ ሲመታ ተከላካዩ ጊት ጋትኩት ለማውጣት ሲጥር ራሱ መረብ ላይ ኳሷን አሳርፏታል።

ሲዳማዎች ጎል ካስተናገዱ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግፌ ዓለሙ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ያቀበለውን ኳስ ዳመነ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ ከወጣችበት ሙከራ ውጭ ጨዋታው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ቡና ቁጥጥር ስር ውሎ የቀጠለ ነበር።

በጥሩ ንክኪዎች ሳጥን ጠርዝ በቀላሉ የሚደርሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በዚህ የጨዋታ መንገድ ጎል አክለዋል።

74ኛው ደቂቃ ላይ ከዋሳዋ መነሻን ያደረገች ኳስን ብሩክ አሾልኮ ሲያቀብለው አብዱልከሪም ወርቁ ግብ ጠባቂው መክብብን በግሩም መንገድ አሳልፎ ሁለተኛዋን ጎል ከመረብ አሳርፏል።

የተጫዋች ለውጥን ቢያደርጉም የተጋጣሚያቸውን ጫና ለመቋቋም የከበዳቸው ሲዳማ ቡናዎች 85ኛው ደቂቃ ሶስተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል።

በጨዋታ ድንቅ የነበረው መስፍን ታፈሠ ከግራ መሬት ለመሬት ወደ ግብ ያሻገረለትን ኳስ ብሩክ በየነ በማስቆጠር የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ በማድረግ ቡድኑ ጨዋታውን 3-0 በሆነ ውጤት እንዲቋጭ አስችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን መቆጣጠር እንደቻሉ ጎል እስኪያስተናግዱም ድረስ በጨዋታው የጎል ዕድልን መፍጠራቸውንም ጠቁመው ከተቆጠረባቸው በኋላ ግን ጨዋታውን መቆጣጠር እንደከበዳቸው እና መከላከልም ላይ ደካማ መሆናቸው ተናግረዋል በአንፃሩ የኢትዮጵያ ቡናው አቻቸው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ ነበር ካሉ በኋላ ከዕረፍት በፊት አየሩ እንዳለ ሆኖ ተጋጣሚያቸው በመልሶ ማጥቃት የተሻለ መሆኑን ጠቁመው ከዕረፍት በኋላ ግን በመነጋገር አንድ ካስቆጠርን እንደምንደግም ባወራነው መሠረት ወደ ሜዳ ገብተን ውጤት ይዘን ወጥተናል ሲሉ ተደምጠዋል።