ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ሁለቱም የዛሬ ጨዋታዎች በአቻ ተጠናቀዋል

በምድብ “ለ” በሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ውሎ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ደብረ ብርሃን ከተማ ከቦዲቲ ከተማ እና ኦሜድላ ከባቱ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።


በመጀመሪያው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በደብረ ብርሀን ከተማ በኩል የጨዋታው መጀመሪያ አካባቢ አለመረጋጋት ተስተውሏል። ቦዲቲ ከተማዎች ኳስን በመቆጣጠር ረገድ ብልጫ ወስዶ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በ12ኛው ደቂቃ የቦዲቲ ከተማ ተጫዋች የሆነው ሰለሞን ደጀኔ ከመሀል ሜዳ አቆራርጦ በመሄድ ወደ ተቃራኒ ግብ አክርሮ በመምታት የግቡን ቋሚ መቶ ወደ ግብ ሳይቀየር ለጥቂት መውጣት ችሏል። ደብረ ብርሀን ከተማ ወደ ጨዋታው በመመለስ በ15ኛው ደቂቃ የደብረ ብርሀን የፊት መስመር ተጫዋቾች የቦዲቲ ከተማ ግብ ጠባቂ ላይ ጫና በመፍጠር በተፈጠረ ስህተት አዲስዓለም ደሳለኝ ያገኘውን ኳስ በቀላሉ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ቦዲቲ ከተማ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ ደብረ ብርሀን ከተማ ኳስን አረጋግቶ ለመጫወት ሲሞክር ተስተውሏል። አጋማሹም በዚው እንቅስቃሴ ምንም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በደብረ ብርሀን ከተማ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቦዲቲ ከተማ የበላይነት በመውሰድ እና ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። በአንፃሩ ደብረ ብርሀኖች የወሰዱትን የግብ የበላይነት ለማስጠበቅ ጥንቃቄን አብዝተው ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በ53ኛው ደቂቃ የቦዲቲ ከተማ ተጫዋች የሆነው ኤፍሬም አበራ ለመልካሙ ቦጌ ግልፅ ኳስ አመቻችቶ በማቀበል በቀላሉ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ብዙ የግብ ሙከራ ሳይደረግ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 8:00 ሰዓት ላይ የተደረገው መርሐግብር ኦሜድላን ከባቱ ከተማ አገናኝቶ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ባቱ ከተማዎች ተሽለው በመገኘት እና መስመሮችን በመጠቀም የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት አርገዋል። በአንፃሩ ኦሜድላ ኃይል የቀላቀለ ረጃጅም ኳስን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያረጉ ተስተውሏል። በ15ኛው ደቂቃ የባቱ ከተማ ተከላካይ የሆነው ተስፋሁን ተሾመ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች ላይ ጥፋት ሠርቷል ተብሎ በመሀል ዳኛው የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሰይፈ ዛኪር አስቆጥሮት ኦሜድላን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ባቱ ከተማ ፈጣን እና ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ባደረጉት ጥረት በ25ኛው ደቂቃ አቤኔዘር ሕዝቅኤል በተጨራረፈ ኳስ ለባቱ ከተማ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ባቱ ከተማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጫና ቢፈጥሩም የኦሜድላ ተከላካይ ክፍል ኳስን ከግብ ክልላቸው በማራቅ ጫናውን ተቋቁመዋል። በ39ኛው ደቂቃ ባቱ ከተማ በፈጣን ሽግግር ከጥልቀት ጆንቴ ገመቹ ያሻገረውን ኳስ ዮናስ አቡሌ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ቢያስቆጥረውም ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ምክኒያት ግቡ ሊሻር ችሏል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ እንቅስቃሴን ተመልክተናል። ኦሜድላ ግብ ለማስቆጠር በመስመር እና በረጃጅም ኳስ ቢሞክሩም የባቱ ከተማን የተከላካይ መስመር ማለፍ ተስኗቸው ሲቸገሩ ተመልክተናል። በአንፃሩ ባቱ ከተማ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ተጋጣሚው ላይ ጫና ሲፈጥርም ተስተውሏል። ሆኖም ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።