የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | ቦሌ ክ/ከተማ መሪነቱን ተረክቧል

ዛሬ በተደረጉ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ሲጥል ቦሌ ክ/ከተማ በሰፊ ግብ ልዩነት በማሸነፍ መሪነቱን በድጋሚ ተረክቧል።

ረፋድ 3:00 ላይ በተደረገው መርሐግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከድሬዳዋ ከተማ ተገናኝተው ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

በመጀመሪያ አጋማሽ ጠንካራ ሆኖ የገባው ድሬዳዋ ከተማ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ነበር። እንዲሁም ቀድሞ ግብ ማስቆጠርም ችሏል። የኳስ ብልጫቸውን በሚገባ የተጠቀሙት ድሬዎች በአንድ ለአንድ ቅብብል ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲደርሱ ለመመልከት ተችሏል።

በ24ኛው ደቂቃ ድሬዎች በአንድ ለአንድ ቅብብል ኳስን ይዘው በመግባት በቁምነገር ካሳ አማካኝነት ወደግብነት ቀይረው መምራት ችለዋል። ግብ ካስቆጠሩም በኋላ ወደኋላ በመመለስ ነጥባቸውን ለማስጠበቅ በመከላከል ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ግብ ቢቆጠርባቸውም ወደ ጨዋታው በመመለስ ጫና ፈጥረው የተጫወቱትን የኤሌክትሪኮችን ጫና መቋቋም የቻሉት ለ12 ደቂቃዎች ብቻ ነበር።

ኤሌክትሪኮች ኳስን ይዘው በሚሄዱበት ቅፅበት የድሬዳዋ ተከላካዮች በሠሩት ጥፋት ከግብ ክልል ትንሽ ራቅ ብሎ ቅጣት ምት አግኝተዋል። ያገኙትንም ቅጣት ምት ምርቃት ፈለቀ አክርራ በመምታት ከመረብ ጋር አገናኝታ አቻ እንዲሆኑ አስችላለች። በዚህ ውጤትም ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ሆኗል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ኤሌክትሪኮች ጠንከር ብለው መመለስ ችለዋል። ጫና ፈጥረው ሦስት ነጥብ ለማሳካት ሲጫወቱም ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ድሬዎች ወደኋላ በመሳብ አንድ ነጥብ ለማሳካት በመከላከላቸው ግባቸውን መድፈር ተስኗቸዋል። በተደጋጋሚ የግብ ሙከራም በኤሌክትሪኮች በኩል ለመመለከት ተችሏል።

ተቀይራ በገባችው በሽታዬ ሲሳዬ ላይ መድረሻቸውን ያደረጉ ኳሶችን በመጣል ኤሌክትሪኮች ቶሎ ቶሎ ወደ ተቀራኒ ቡድን ግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ግን ተስኗቸዋል። በዚህም ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊገባደድ ችሏል።

የ10:00 ሰዓቱ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስን ከቦሌ ክ/ከተማ አገናኝቶ ቦሌ ክ/ከተማ በሰፊ ግብ ልዩነት አሸንፏል።

በተደጋጋሚ ሽንፈት እያስተናገደ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬም ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን በሊጉ ሁነኛ ተፎካካሪ የሆነው ቦሌ ክ/ከተማ ጨዋታው እንደተጀመረ ጫና ፈጥሮባቸዋል። በተደጋጋሚም የግብ ማግባት ሙከራ ሲያድርጉ ተስተውለዋል።


በ10ኛው ደቂቃ ላይ ቦሌዎች በእርስ በርስ ቅበብል በመግባት የመጀመሪያ ግብ በሜላት ጌታቸው አማካኝነት አስቆጥረዋል። በድጋሚም ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉት ቦሌዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር 16 ደቂቃ ጠብቀዋል። በ26ኛው ደቂቃ ፍሬሕይወት በራሷ ጥረት ግብ በማስቆጠር 2ለ0 እንዲመሩ ሆኗል።

በዚህ ብቻ ያላበቃው ቦሌ ክ/ከተማ በ33ኛው ደቂቃ ትዕግስት ወርቄ ከማዕዘን ምት የተገኘውን ኳስ በግንባሯ ገጭታ በማስቆጠር መሪነታቸውን አስፍታለች። ቦሌዎች ግብ አስቆጥረው ደስታቸውን እየገለፁ በሚዘናጉበት ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ34ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተጣለላትን ኳስ ምስራቅ ዛቶ ከመረብ አገናኝታ 3ለ1 እንዲሆኑ አድርጋለች።

የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ተጨማሪ ሊታይ ሲል በ45ኛው ደቂቃ ሜላት አሊሙዝ ሌላኛውን ድንቅ ግብ ለቦሌዎች አስቆጥራ 4ለ1 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ሆኗል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ የተቀዛቀዘ ጨዋታ ለማየት ተችሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ሲያደርግ የተስተዋለ ቢሆንም ጠንካራውን የቦሌ ክፍለ ከተማ ተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ለማስቆጠር ሲቸግራቸው ታይተዋል።

በ61ኛው ደቂቃ የማዕዘን ምት ያገኙት ቦሌዎች ቀጥታ ወደ ግብ አሻምተውት ይዲዲያ አጨ ከመረብ ጋር አገናኝታ 5ለ1 በማድረግ ጨዋታውን ወደ መጨረስ ደርሰዋል። በዚህም ተጨማሪ ሁነኛ ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው በቦሌ ክ/ከተማ 5ለ1 አሸናፊነት ተገባዷል።