ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል አድርገዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ሲጀምሩ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገው አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

ቀን 8:00 ላይ ሀምበርቾ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ተገናኝተው አዲስ አበባ ከተማ 3-1 ድል አድርገዋል። አዲስ አበባ ከተማ የጨዋታ በላይነት ባሳየበት በዚህ ጨዋታ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ገና ጨዋታው እንደጀመረ ማሳየት ችለዋል።እንዲሁም በኳስ ቁጥጥር ሙሉ ለሙሉ ብጫ የወሰዱበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል። ሀምበርቾ በአንፃሩ ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ለማሳለፍ ተገደዋል። የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት አዲስ አበባ ከተማዎች ኳስን መሃል ሜዳ አከባቢ መስርተው በእርስ እርስ ቅብብል ወደተጋጣሚው ግብ ክልል ሲገቡ ተስተውለዋል።

በርከት ያለ የግብ ማግባት ሙከራ ካደረጉ በኋላ የጥረታቸው ውጤት የሆነችዋን ግብ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነችዋ አይናለም አለማየሁ በ13ኛው ደቂቃ በመስመር በኩል ኳስን በራሷ ጥረት ይዛ በመግባት ከመረብ ጋር አገናኝታ መሪ እንዲሆኑ አስችላለች። እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የፈጀባቸው አምስት ደቂቃ ብቻ ነበር። ሀምበርቾዎች ግብ ተቆጥሮባቸው መረጋጋት ተስኗቸው ስህተት ሲሰሩ የታዩ ሲሆን የመጀመሪያ ግብ ከተቆጠረ ከ5ኛ ደቂቃ በኋላ በ18ኛው ደቂቃ የማዕዘን ምት ያገኙት አዲስ አበባዎች ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ የተከላካይ መስመር ተጫዋች የሆነችዋ ሰብለ ቶጋ በግንባሯ ገጭታ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር 2ለ0 እንዲመራ ሆኗል። አዲስ አበባዎች በተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራ ሲያድርጉ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ሀምበርቾዎች ጠንከር ብለው ለመግባት የተጫዋች ቅያሪ አድርገዋል። የሁለተኛ አጋማሽ እንደተጀመረ በ46ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው መንደሪን ታደሰ ግብ በማስቆጠር ሀምበርቾዎችን ወደጨዋታው ለመመለስ ጥረት እንዲያደርጉ አድርጋለች። በዚህም ወደጨዋታው በመመለስ ኳስን ተቆጣጥረው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን በ52ኛው ደቂቃ ቤተልሔም መንተሎ በእርስ በእርስ ቅበብል የተገቺዋን ኳስ በሀምበርቾ መረብ ላይ ማሳረፏ አዲስ አበባዎች የጨዋታ ብልጫ እንዲወስዱ አድርጋለች። አዲስ አበባ ከተማዎች መድረሻቸው በዓይናለም አለማየሁ ላይ ያደረጉ ኳሶችን በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ግን ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት ጨዋታው በአዲስ አበባ 3ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

10:00 ላይ ይርጋጨፌ ቡናን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘውን መርሃግብር ኤሌክትሪክ 2-0 አሸንፏል። በመጀመሪያዎቹ 35 ደቂቃዎች ተመጣጠኝ በነበረው ጨዋታ ይርጋጨፌዎችም ሆኖ ኤሌክትሪኮች እምብዛም ለግብ የተቃረበ የግብ ሙከራ አላደርጉም። ቢሆንም ኤሌክትሪክ በኳስ ቁጥጥር ከተጋጣሚው በልጦ በመገኘት የግብ ለማግባት ጥረት አድርገዋል። ይርጋጨፌ ቡና በአንፃሩ ግብ እንዳይቆጠርባቸው ወደኋላ በመመለስ ሲከላከሉ ተስተውለዋል።

በ35ኛው ደቂቃ የምስራች ላቀው በራሷ ጥረት ኳስን ይዛ ወደ ግብ ክልል በመግባት ለኤሌክትሪክ ግብ አስቆጥራ 1ለ0 እንዲመሩ አድርጋለች። ግብ መቆጠሩ ጨዋታው ወደ አንድ ጎን እንዲያደላ ያደረገ ሲሆን ኤሌክትሪኮች የሚያገኙትን አጋጣሚዎች ወደ ግብ ለመቀየር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ግን ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1ለ0 መሪነት አጋምሰዋል።

ከእረፍት መልስ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጫና ፈጥረው ሲጫዎቱ ይርጋጨፌዎች በአንፃሩ ተጨማሪ ግብ እንዳይቆጠርባቸው ሲከላከሉ ታይተዋል። ለኤሌክትሪኮች የሽታዬ ሲሳይ ተቀይራ መግባት ኳሶች ወደፊት ሲጫወቱ መዳረሻቸው እሷ ላይ እንዲሆን አድርጓል። በ67ኛው ደቂቃ ሽታዬ ሲሳይ ኳስን ይዛ የይርጋጨፌ ቡናን ተከላካዮች አታላ ለማለፍ በሚታደርግበት ግዜ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሷ ሽታዬ ሲሳይ መጥታ በማስቆጠር መሪነታተውን አጠናክራ ጨዋታውም በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።