ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | አዲስ አበባ ከተማ ልዩነቱን ማጥበብ የሚችልበትን ዕድል አምክኗል

የኢትዮጵያ ወንዶች ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የ15ኛ ሳምንት ዛሬ ቀጥሎ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ኦሮሚያ ፖሊስ አዲስ አበባ ከተማን ሲያሸንፍ ጅማ አባ ጅፋር እና ኮልፌ ቀራኒዮ ነጥብ ተጋርተዋል።

3:00 ላይ በጀመረው መርሃግብር ኦሮሚያ ፖሊስ አዲስ አበባ ከተማን ገጥሞ ኦሮሚያ ፖሊስ በመጀመሪያ አጋመሽ እና በሁለተኛ አጋማሽ ባስቆጠሩት ግቦች 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ሳቢ በነበረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል በመግባት የግብ ማግባት ሙከራ ሲያድርጉ ታይተዋል። በመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት ኦሮሚያ ፖሊሶች ገና በ6ኛው ደቂቃ ዳንኤል ዳርጌ በእርስ በርስ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ኦሮሚያ ፖሊን ቀዳሚ አድርጓል።

አዲስ አበባ ከተማዎች ግብ ከተቆጥሮባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተረጋግተው ኳስን መስርተው ሲጫውቱ ተስተውለዋል። በዚህም በርከት ያለ ግብ የማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። ሆኖም ግን ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በኦሮሚያ ፖሊስ 1ለ0 መሪነት ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ሁለቱም ቡድኖች ጠንከር ብለው በመግባት ማራኪ አጨዋወት ለተመልካች አስመልክተዋል። በ59ኛው ደቂቃ ዳንኤል ዳርጌ ሁለተኛ ግብ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ የኦሮሚያ ፖሊስ መሪነትን አጠናክሯል። አዲስ አበባ ከተማ በአንፃሩ ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ የተቀዛቀዘ አጨዋወት አስመልክተዋል።

በ80ኛው ደቂቃ የተከላካይ መስመር ተጨዋች የሆነው ይሁን ገልግሌ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ወደጨዋታ እንዲመለሱ አድርጓል። ሆኖም ግን በኦሮሚያ ፖሊስ 2ለ1 መሪነት መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል። አዲስ አበባ ከተማዎች ኳስን ይዘው አቻነት ግብ ለማስቆጠር በሚገቡበት ቅፅበት በመልሶ ማጥቃት ዳንኤል ዳርጌ ጭማሪ በታየው ደቂቃ ውስጥ ሦስተኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በኦሮሚያ ፖሊስ አሸናፊነት ተገባዷል።

በማስከተል የተረገው የ5:00 የተደረገው ጅማ አባ ጅፋርን ከኮልፎ ቀራኒዮ ያገናኘው መርሃግብር ያለ ግብ ተጠናቋል።

እምብዛም ለግብ የተቃረበ ሙከራ ያላሳየው የ5 ሰዓቱ ጨዋታ ያለግብ ሲጠናቀቅ ኮልፌዎች በመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ነበር።ጅማ አባ ጅፋር በአንፃሩ በመጀመሪያ አጋማሽ በመልሶ ማጥቃት ወደግብ ክልል ለመግባት ጥረት ቢያድርጉም ጠንከር ብሎ የዋለውን የኮልፌዎችን ተከላካይ መስመር አልፎ ግባቸውን መድፈር ተስኗቸዋል።

ኮልፌዎች ኳስን መሰርተው በመጫወት ከተከላካይ መስመር በሚነሱ ኳሶች ተደግፈው ቶሎ ቶሎ ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ግብ በፍፁም አልቻለም። በዚህ የተገደዱት ሁለቱም ቡድኖች ያለምንም ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ቀዝቀዝ ያለ ጨዋታ ታይቷል። በዚህም በግብ ሙከራዎች ሁለቱም ቡድኖች ደካማ ነበሩ። እንዲሁም ጥሩ የማይባል እንቅስቃሴ አድርገዋል። ጅማዎች ግልፅ ለግብ የተቃረበ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ኮልፌዎችም እንዲሁ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ ሳያመክኑ ታይተዋል። ጨዋታውም ያለግብ ሊጠናቀቅ ተገዷል።