ሪፖርት| ማራኪ ያልነበረው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ

የሀድያ ሆሳዕናና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ በሳምንቱ የተመዘገበ የመጀመርያ የአቻ ውጤት ሆኗል።

ወልቂጤዎች ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ወንድማገኝ ማዕረግ በመሳይ ጳውሎስ ተክተው ሲገቡ ሀድያዎች በበኩላቸው ከንግድ ባንክ አቻ ከወጣው ቋሚ አሰላለፍ መለሰ ሚሻሞና አስጨናቂ ፀጋዬ በግርማ በቀለና ቴዎድሮስ ታፈሰ ለውጠው ገብተዋል። ከጨዋታው ቀደም ብሎ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ገብቶ የነበረው ሰመረ ሀፍታይ ትጥቅ ባለማሟላቱ በሳሙኤል ዮሐንስ ተተክቷል።

ቀዝቃዛና ጥቂት የግብ ሙከራዎች በታዩበት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢይዙም የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የነበረው ግን ወልቂጤ ከተማ ነበር። ጋዲሳ መብራቴ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉት ሰራተኞቹ በተጠቀሰው መስመር የግብ ዕድሎችም ፈጥረዋል። በተለይም ጋዲሳ መብራቴ ተጫዋች አልፎ ወደ ሳጥን አሻግሮት ተመስገን በጅሮንድ ሳይጠቀምበት የቀረው ዕድል ቡድኑ ከፈጠራቸው ዕድሎች የተሻለው ነበር። ሰራተኞቹ በፍጥነት ዘገም ባለው ሽግግር ምክንያት የሀድያን የተከላካይ መስመር አልፈው በርካታ ዕድሎች መፍጠር ባይችሉም በብዙ መለክያዎች ከተጋጣሚያቸው የተሻለ አጋማሽ አሳልፈዋል። በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎችም በሙላለም መስፍን አማካኝነት ሁለት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በአጋማሹ በቁጥር በዝተው ጥቃቶች ከመመከት አልፈው ይህ ነው የሚባል ተጋጣሚን ለአደጋ የሚያጋልጥ የማጥቃት አጨዋወት ያልነበራቸው ሀድያዎች የፈጠሯቸው ዕድሎች ጥቂት ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ተመስገን ብርሀኑ ከሳጥኑ ጠርዝ መቷት ግብ ጠባቂው ፋሪስ ያዳናት ኳስ ትጠቀሳለች።

ሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት የተሻለ ፉክክር ቢታይበትም በሙከራ ረገድ ግን ተመሳሳይ ነበር። በአጋማሹ ሀድያ ሆሳዕናዎች ከመጀመርያው አጋማች በውስን መልኩ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት አሳይተው ሁለት ጥራት ያላቸውን ሙከራዎች ማድረች ችለዋል። እንደመጀመርያው አጋማሽ ኳስ ተቆጣጥረው የተጫወቱት ወልቂጤ ከተማዎች በበኩላቸው በቆሙ ኳሶች ከፈጠሯቸው ዕድሎች ውጭ ብልጫውን ተጠቅመው በዛ ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም።

በአጋማሹ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ተመስገን ብርሀኑ ዳዋ ሆቴሳ በመልሶ ማጥቃት ይዟት የሄደው ኳስ ተቀብሎ መቷት ግብ ጠባቂው የመለሳት እንዲሁም በየነ ባንጃ ከሳጥን ውጭ መቷት በተመሳሳይ ግብ ጠባቂው ፋሪስ የመለሳት ኳስ ይጠቀሳሉ፤ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ይዘው የጠሩ ዕድሎች መፍጠር ባልቻሉት ወልቂጤዎች በኩል ደግሞ ተቀይሮ የገባው ሳምሶን ጥላሁን ከቀኝ መስመር የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ ሞክሯት ከድር ኩሉባሊ ተደርቦ ያወጣት ሙከራ ትጠቀሳለች።

ማራኪ ያልሆነ እንቅስቃሴና ጥቂት የግብ ሙከራ ያስመለከተን ጨዋታ ባዶ ለባዶ መጠናቀቁ ተከትሎ በጨዋታ ሳምንቱ የተመዘገበ የመጀመርያው ግብ አልባ ጨዋታ ሆኗል።