ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ስልጤ ወራቤ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ድል ቀንቷቸዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 17ኛ ሳምንት በመጀመሪያ ቀን በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀምር በምድብ “ሀ” ስልጤ ወራቤ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

ረፋድ ሦስት ሰዓት ላይ ሞጆ ከተማን ከስልጤ ወራቤ በተገናኙበት ጨዋታ ስልጤ ወራቤ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችች ባስቆጠሩት ግብ አሸናፊ ሆነዋል። በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች በተረጉበት በዚህ ጨዋታ ሞጆ ከተማ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ነበሩ። ስልጤ ወራቤም በመልሶ ማጥቃት አንዳንድ የሚያገኙትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙ ቀርተው የመጀመሪያ አጋማሽ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እየተቀዛቀዘ የመጣ ሲሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር እምብዛም የግብ ሙከራዎች አልታዩበትም። ሁለቱም ቡድኖች ግብ ከማስቆጠር ይልቅ ነጥብ ለመጋራት ወደኋላ አፈግፍገው በመከላከል ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን በ84ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ብቸኛ አጋጣሚ ስልጤ ወራቤዎች ተጠቅመዋል። ተቀይሮ የገባው ጉልላት ተስፋዬ የሞጆን ተከላካዮች አታልሎ በማለፍ ያለቀ ኳስ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ለነበረው ለምንተስኖት መንግሥቱ አሻግሮለት ምንተስኖት መንግሥቱ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ጋር አገናኝቶት ስልጤ ወራቤ ሶስት ነጥብ እንዲያሳካ አድርጓል።

የዖለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በንብ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ መካከል ተደርጎ ኮልፌ በሁለቱም አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች አሸንፈዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ንቦች የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር። ሆኖም ግን በመልሶ ማጥቃት ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ያደረጉት ኮልፌዎች ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ነበሩ። በ15ኛው ደቂቃ የመሃል ሜዳ ስፍራ ተጫዋች የሆነው በድሉ መርድ መሃል ሜዳ አከባቢ ሆኖ አክርሮ በመምታት ባስቆጠራት ግብ ኮልፎዎች 1ለ0 እየመሩ ዕረፍት መውጣት ችለዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ ወደ ኮልፌ ዞሮ ለመመለከት ተችሏል። ንብ በአንፃሩ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር የተዳከመ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በ52ኛው ደቂቃ ተስፋዬ ፍላቴ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ለኮልፌ መሪነቱን አስፍቷል። ሁለተኛ ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ውጤቱን ለማስጠበቅ ኮልፌዎች በሙሉ ወደኋላ በመመለስ ሲከላከሉ ለማየት ተችሏል።

በ67ኛው ደቂቃ ኢዮብ ደረሰ በንክኪ የተገኘችውን ኳስ ለንብ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ጨዋታውን 2ለ1 ማድረግ ችሏል። በዚህም ንብ ወደ ጨዋታ በመመለስ ጥሩ በመንቀሳቀስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ለመመለከት ተችሏል። ሆኖም ግን ኮልፌዎች የተከላካይ መስመራቸውን በመዝጋታቸው ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል። በዚህም ጨዋታው በኮልፌ 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።