ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ነጌሌ አርሲ ጣፋጭ ድል ተቀዳጅቷል

በምድብ “ለ” የሁለተኛው ዙር የሶስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሸገር ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ነጥብ ሲጋሩ ነጌሌ አርሲ ሙሉ ሶስት ነጥብ አሳክቷል።

ረፋድ 3:00 ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻ እና ሸገር ከተማ ያለ ምንም ግብ ነጥብ ተጋርተዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ እና ብዙም ሳቢ ያልሆነ ጨዋታ ተመልክተናል። በኳስ ቁጥጥር ብልጫው ሸገር ከተማ የበላይነቱን የወሰደ ቢሆንም ተጋጣሚ ቡድን ላይ አደጋ መፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ወሎ ኮምቦልቻም ወደራሱ ግብ አፈግፍጎ በመጫወት የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል ለመፍጠር በዮናታን ኃይሉ አማካኝነት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያረጉም ለግብ መቅረብ ተስኗቸዋል። አጋማሹም በዚሁ አጨዋወት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ለዐይን ሳቢ ያልሆነ እና ጥንቃቄ የበዛበት አጨዋወትን ተመልክተናል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል የኳስ መቆራረጥ ታይቶባቸዋል። በጨዋታውም አስደንጋጭ የግብ ሙከራ ሳንመለከት ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 5:00 ላይ በተደረገው መርሐግብር ነጌሌ አርሲ ደሴ ከተማን አሸንፏል።


በመጀመሪያው አጋማሽ ደሴ ከተማ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ ለመጫወት የሞከረ ሲሆን በአንፃሩ ነጌሌ አርሲ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የደሴ የግብ ክልልን ሲያስጨንቁ ተስተውሏል። ሆኖም በአጋማሹ ከፍተኛ አደጋ የሚፈጥር የግብ ሙከራ ሳንመለከት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ  ሁለቱም ቡድኖች ራሳቸውን አጠናክረው ገብተው ጥሩ አጨዋወት ተመልክተናል። በ52ኛው ደቂቃ የነጌሌ አርሲው ተጫዋች ምንተስኖት ተስፋዬ ከመስመር በመነሳት የደሴ ተከላካይን በማታለል ለሰለሞን ገመቹ በማቀበል ሰለሞን ገመቹ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ነጌሌ አርሲ በመነቃቃት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት በማድረግ በ58ኛው ደቂቃ ገ/መስቀል ዱበሌ ከጥልቀት በመነሳት መሀል ሜዳውን አቆራርጦ በመሄድ የፈጠረውን የግብ ዕድል ጀቤሳ ሚኤሶ ወደ ግብነት ቀይሮት የነጌሌ አርሲን መሪነት አጠናክሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የተረበሹት የደሴ ከተማ ተጫዋቾች በመረጋጋት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።  በ87ኛው ደቂቃ በደሴ ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው ኢብራሒም ከድር ወደ ግብ ተመትቶ የተመለሰውን ኳስ ቢያስቆጥርም ቡድኑን ከሽንፈት መታደግ ተስኖት ጨዋታው በነጌሌ አርሲ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።