መረጃዎች | 74ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉ ውድድር ከቀናት ዕረፍት በኃላ ነገ በ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይመለሳል ፤ እኛም ነገ የሚደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልኩ አቅርበናል።

መቻል ከወላይታ ድቻ

የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ መርሃግብር በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙትን መቻሎችን ድል ከናፈቃቸው ወላይታ ድቻዎች የሚያገናኝ ይሆናል።

በሰላሳ ስድስት ነጥቦች ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ ነጥብ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ደግሞ በእኩል ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጠው በሰንጠረዡ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት መቻሎች ከተፎካካሪዎቻቸው ቀድመው ጨዋታቸውን እንደማድረጋቸው ይህን ጨዋታ በድል መወጣት ዳግም ወደ ሰንጠረዡ አናት እንደሚመልሳቸው በማሰብ የሚያደርጉት ነው።

በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት አሁን ላይ በሰንጠረዡ አናት ከሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እጅግ ወሳኝ መርሃግብር የሚጠብቃቸው መቻሎች የነገውን ጨዋታ ድል ማድረጋቸው ቀጣይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚኖራቸውን ጨዋታ ዋጋ ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑ አንፃር ለእነሱ ወሳኝነት አለው።

በመጨረሻ አምስት የሊግ መርሃግብሮች በአንዱም ድል ማድረግ ያልቻሉት ወላይታ ድቻዎች ከእነዚሁ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥብ ሶስቱን ብቻ ሲያሳኩ ይህም በሃያ አራት ነጥብ በሰንጠረዡ ወደ አስራ አንደኛ ደረጃ እንዲንሸራተቱ አድርጓቸዋል።

በሊጉ ባደረጓቸው አስራ ስምንት ጨዋታዎች በፍትሃዊነት ለድል ፣ ለአቻ እና ሽንፈት ያከፋፈሉት ወላይታ ድቻዎች በነገው ጨዋታ ከናፈቁት ድል ጋር ለመታረቅ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በመቻል በኩል አዲስ ፈራሚው አብዱ ሙታላቡ ኡታራን ከቶጎ ብሔራዊ ቡድን መልስ በቂ ዝግጅት ባለማድረጉ ለነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩል ተከላካዩ አንተነህ ጉግሳ እና አጥቂው ቢኒያም ፍቅሬ በቅጣት ምክንያት የነገውም ጨዋታ የሚያመልጣቸው ይሆናል።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ አስራ ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ስምንት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻሎች ደግሞ በአራት ጊዜ አሸንፈው በቀሪዎቹ አምስት ግንኙነቶች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ። የጦና ንቦቹ አስራ ሰባት እንዲሁም ጦሩ ደግሞ አስራ ሦስት ግቦችን በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ማስቆጠር ችለዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ

የምሽቱ ተጠባቂ መርሃግብር ደግሞ በአንድ ነጥብ ልዩነት በሰንጠረዡ ከመሪዎቹ በጥቂት ርቀት የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኝ ነው።

ከአስደናቂ ግስጋሴያቸው ማግስት በሊጉ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈትን ያስተናገዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሰንጠረዡ አናት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ራሳቸውን ለመመለስ በፍጥነት ወደ ድል መመለስ ያሻቸዋል።

አሁን ላይ በሃያ ዘጠኝ ነጥቦች አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች የነገው ጨዋታ ከእነርሱ በአንድ ነጥብ ብቻ ልቆ በአራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ፋሲል ከነማ ጋር የሚደረግ መሆኑ ተጨማሪ መነሳሻ እንደሚጥርላቸው ይጠበቃል ፤ በጨዋታው በተለይ በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ፍፁም ተቸግሮ የተመለከትነውን የቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ መሻሻል የግድ የሚለው ይሆናል።

በሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር ከመጀመሪያው አንፃር በተሻለ መንገድ የጀመሩት ፋሲሎች ካደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ የከፈቱ ሲሆን ይህም በሰንጠረዡ ቦታቸውን እንዲያሻሽሉ ረድቷቸዋል።

ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰባት ነጥቦች ርቀው የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በሰንጠረዡ ወደ ላይ ለመጠጋት ከዚህ በኃላ በሚኖሩ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥቦችን መሰብሰብ የግል ይላቸዋል።

በፋሲል ከነማ በኩል በግብ ጠባቂ ስፍራ ከሰሞኑ ለስህተቶች ሲጋለጥ የተመለከትነው እና በባለፈው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ለውጥ ለማድረግ የተገደዱት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ጨዋታ ለማሊያዊው ሳማኪ ሜክኤል ቅድሚያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል መሐመድኑር ናስር እና ጫላ ተሺታ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆናቸው ሲረጋገጥ በፋሲል ከነማ በኩል የጌታነህ ከበደ ፣ ዓለምብርሃን ይግዛው እና አምሳሉ ጥላሁን በነገው ጨዋታ የመሰለፋቸው ነገር ሲያጠራጥር አፍቅርቶ ሰለሞን የነገው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት እንደሚያመልጠው ተረጋግጧል።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ እስካሁን አስራ አራት ጊዜ የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ያደረጉ ሲሆን ፋሲል ከነማ አምስት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሦስት ድሎችን ሲያሳኩ ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል። ፋሲል ከነማዎች በእነዚህ ጨዋታዎች አስራ አራት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ አስራ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)