ሪፖርት | መቻል ተከታታይ ድል ተቀዳጅቷል

በሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር መቻሎች በምንይሉ ወንድሙ ብቸኛ ግብ የጦና ንቦቹን 1ለዐ ረተዋል።

በሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር መቻል እና ወላይታ ድቻ ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች ከ18ኛ ሳምንት ጨዋታቸው በተመሳሳይ የአንድ የመሃል ተከላካይ ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ንግድ ባንክን 2ለ0 አሸንፈው የመጡት መቻሎች የአንድ ጨዋታ ቅጣት ላይ የነበረውን አስቻለው ታመነን በስቴፈን ባዱ አኖርኬ ቀይረው ሲያስገቡ ከኢትዮጵያ መድን ጋር 2ለ2 በተለያዩት ድቻዎች በኩል በቀይ ካርድ በተሰናበተው አንተነህ ጉግሳ ምትክ መልካም ቦጋለ በቋሚ አሰላለፍ ተካቷል።


ቀን 9 ሰዓት ሲል በትናንትናው ዕለት ሕይወቱ ላለፈው የባህር ዳር ከተማው አማካይ አለልኝ አዘነ የአንድ ደቂቃ የሕሊና ጸሎት በማድረግ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ሜዳው ላይ ቀድሞ በጣለው ዝናብ ሜዳው መጠነኛ ውሃ በመቋጠሩ በሁለቱም በኩል የተደራጀ እንቅስቃሴ ለማየት አልቻልንም ነበር።

መሃል ሜዳው ላይ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ያደረጉት መቻሎች 31ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሽመልስ በቀለ ከአስቻለው ታመነ በረጅሙ በተሻገረለት ኳስ በሳጥኑ የግራ ክፍል ገብቶ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ምንይሉ ወንድሙ በጥሩ አጨራረስ ግብ አድርጎታል።

በሁለቱም በኩል ግለቱ ይቀዛቀዝ እንጂ አንጻራዊ ብልጫ መውሰድ የቻሉት መቻሎች 42ኛው ደቂቃ ላይም ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው አስቻለው ታመነ ከረጅም ርቀት ያሻገረውን ኳስ ወደ ሳጥን ቀድሞ በመግባት ያገኘው ዮሐንስ መንግሥቱ ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስ ወላይታ ድቻዎች በተሻለ ግለት ጨዋታውን ጀምረው በቁጥር እየበዙ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መታተራቸውን ቢቀጥሉም የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራ ግን በመቻሉ አማካይ ሽመልስ በቀለ አማካኝነት ተደርጎ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ተቆጣጥሮታል።


የጦና ንቦቹ በፈጣን ሽግግር ለማጥቃት ከነበራቸው ፍላጎት ወጥተው ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያ ሰጥተው ለመጫወት ቢሞክሩም ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ሲቸገሩ መቻሎች በአንጻሩ 63ኛው ደቂቃ ላይም ወሳኝ የግብ ዕድል ፈጥረው ግሩም ሀጎስ ከቀኝ መስመር ድንቅ በሆነ ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ሳያገኘው ቀርቷል።

ጨዋታው 72ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ወላይታ ድቻዎች የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን አድርገዋል። አበባየሁ ሀጂሶ ተቀይሮ የገባው ኢዮብ ተስፋዬ ባመቻቸለት ኳስ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት በመምታት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ይዞበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የቀረቡት እና ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ለመጫወት የሞከሩት መቻሎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊቆጠርባቸው ተቃርቦ ኬኔዲ ከበደ ከቀኝ መስመር የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ኢዮብ ተስፋዬ ያደረገው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲወጣበት በአንጻሩ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ የመቻሉ አማካይ ዮሐንስ መንግሥቱ ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መጠነኛ ፉክክር ቢደረግበትም 90+1ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው ባዬ ገዛኸኝ ከረጅም ርቀት ሞክሮት ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ከመለሰበት ኳስ ውጪ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በመቻል 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታቸውን እስኪያደርጉ ድረስ መቻል ሊጉን በ39 ነጥቦች መምራት ጀምሯል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ከጨዋታ ጨዋታ የውጤት ማሽቆልቆል ላይ እንዳሉ አምነው የውድድሩ መቆራረጥ ችግሮችን እንደፈጠረባቸው ዛሬም ሜዳው ውሃ በመያዙ የፈለጉትን ያህል እንዳልተንቀሳቀሱ ጠቁመው በሁለተኛው አጋማሽ በመጠኑ ለመሻሻል መሞከራቸውን ሲናገሩ የመቻሉ ምክትል አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በበኩላቸው የዝናቡ ሁኔታ ሊጫወቱ ካሰቡበት መንገድ እንዳስወጣቸው ጠቁመው ለሻምፒዮንነት ለመጫወት እንደሚያስቡ እና ዋና ትኩረታቸው ግን በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ መሆኑን ገልጸዋል።