ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ድል ተመልሷል

ነብሮቹ በተመስገን ብርሃኑ እና በዳዋ ሆቴሳ ግቦች ሀምበርቾን 2ለ0 ረተዋል።

በምሽቱ መርሐግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና ሀምበርቾ ሲገናኙ ነብሮቹ በ18ኛው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ቃለአብ ውብሸት ፣ ካሌብ በየነ ፣ አስጨናቂ ጸጋዬ እና እንዳለ ዓባይነህ በሄኖክ አርፊጮ ፣ ግርማ በቀለ ፣ ዳግም ንጉሤ እና ቴዎድሮስ ታፈሰ ተተክተው ለጨዋታው ሲቀርቡ ሀምበርቾዎች በአንጻሩ በአዳማ ከተማ 3ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ ምናሴ በራቱ ፣ አዲስ ፈራሚው አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ አቤል ዘውዱ ፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ እና አልዓዛር አድማሱ በምንያምር ጴጥሮስ ፣ ታየ ወርቁ ፣ አብዱልሰላም የሱፍ ፣ ተመስገን አሰፋ እና በኃይሉ ተሻገር ተተክተው በቋሚ አሰላለፍ ተካተዋል።


1 ሰዓት ሲል በቅርቡ ሕይወቱ ላለፈው የባህር ዳር ከተማ አማካይ አለልኝ አዘነ የሕሊና ጸሎት ተደርጎ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሰማ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ሀዲያዎች 3ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን የጠራ የግብ ዕድል ፈጥረው ዳዋ ሆቴሳ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመግባት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ ተቆጣጥሮበታል።

ካለፉት ሳምንታት በመጠኑ የተነቃቃ አጀማመር ያደረጉት ሀምበርቾዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ ባደረጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ ዳግም በቀለ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ጥሩ ሙከራ ግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር መልሶበታል። ሆኖም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ አጥቅተው የተጫወቱት ነብሮቹ ከ21-23ኛው ደቂቃ የፈጠሯቸውን 4 የግብ ዕድሎችን የሀምበርቾው ዲንክ ኪያር በግሩም ብቃት ተከላክሏቸዋል።

መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ የሀምበርቾው አጥቂ ዳግም በቀለ 31ኛው ደቂቃ ላይ ከድር ኩሊባሊ በሠራው ስህተት ባገኘው ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመግባት ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣበት ግለቱ እንደ አጀማመሩ ሳይሆን እየተቀዛቀዘ የሄደው ጨዋታም ያለ ግብ ተጋምሷል።


ከዕረፍት መልስ በተሻለ ንቃት ጨዋታውን የጀመሩት ነብሮቹ 53ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሳሙኤል ዮሐንስ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ዳዋ ሆቴሳ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ እና በግቡ የላይ አግዳሚ ተመልሶበታል። ከአንድ ደቂቃ በኋላም ዳዋ ሆቴሳ ግብ ጠባቂውን ቢያልፈውም ከአዲስዓለም ተስፋዬ ጋር በተፈጠረ ንክኪ ሳይጠቀምበት ሲቀር ዋና ዳኛው በአምላክ ተሰማም የፍጹም ቅጣት ምት ለመስጠት አሳማኝ አልሆነላቸውም።

ጨዋታው 64ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ዳዋ ሆቴሳ ከግራ መስመር መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተመስገን ብርሃኑ በተረጋጋ አጨራረስ በግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ እግር መሃል አሳልፎ (በሎጬ) ማስቆጠር ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደፊት ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ሀምበርቾዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በዳግም በቀለ 76ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በበፍቃዱ አስረሳኸኝ አማካኝነት ከረጅም ርቀት ጥሩ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር አግዷቸዋል።

ሀዲያዎች በቁጥር በዝተው ከራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ ማሳለፍን ሲመርጡ ሀምበርቾዎች ግን 78ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን ወርቃማ የግብ ዕድል ፈጥረው አልዓዛር አድማሱ ከቀኝ መስመር በተሻገረለት ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ በመቆጣጠር ግብ ጠባቂውን አልፎ ማመቻቸት ቢችልም ሙከራውን የመሃል ተከላካዩ ቃለአብ ውብሸት አግዶበት አባክኖታል።

ጨዋታው 87ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ነብሮቹ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። በረከት ወልደዮሐንስ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ የሀምበርቾው የመሃል ተከላካይ ዲንክ ኪያር ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው ዳዋ ሆቴሳ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 5 ደቂቃዎች ውስጥም ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ሊግ የተመለሰው ዑመድ ኡክሪ በዳዋ ሆቴሳ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል። ጨዋታውም በሀዲያ ሆሳዕና 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበርቾው ጊዜያዊ አሰልጣኝ መላኩ ከበደ የሚችሉትን ያህል እንደሞከሩ ነገር ግን እንቅስቃሴያቸው ጥሩ ቢሆንም እንዳልተሳካላቸው እና በመከላከል ክፍተት ግብ ማስተናገዳቸውን ጠቁመው የመሃል ተከላካይ ላይ የሚፈልጉትን ውህደት ለማግኘት እንደተቸገሩ ተናግረዋል። ድል የቀናቸው የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ አለመረጋጋት እንደነበረባቸው እና ያንንም ከዕረፍት መልስ ለማስተካከል እንደሞከሩ በመናገር የነበራቸው ትዕግስት ለድል እንዳበቃቸው እና ከዳዋ ሆቴሳ እና ተመስገን ብርሃኑ ጥምረት ከዚህም በላይ እንደሚጠብቁ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።