ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ቤንች ማጅ ቡና እና ነቀምቴ ከተማ ድል አድርገዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ‘ሀ’ 18ኛ ሳምንት በሁለተኛ ቀን ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል ቤንች ማጅ ቡና እና ነቀምቴ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።

የረፋድ 3:00 ሰዓቱ ጨዋታ ሀላባ ከተማ ከቤንች ማጅ ቡና ተገናኝተው ቤንች ማጅ ቡና በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ሀላባ ከተማ ግን አልፎ አልፎ ኳስ መስርተው ይዘው በመግባት ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም በደካማ አጨራረስ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። እንዲሁም ከተጋጣሚያቸው በላይ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። ቤንች ማጅ ቡናም ግብ ለማስቆጠር አንዳንድ የግብ ሙከራ ቢያደርግም የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ተገባዷል።

ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቅብብል እና የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። እንዲሁም ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ አስመልክተዋል። በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት ሀላባ ከተማዎች ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ ነበሩ። ተቀይሮ የገባው ፎሳ ሳደቦ ከፋሲል አበባየሁ ጋር በአንድ ለአንድ ቅብብል በመግባት በ56ኛው ደቂቃ ኳስና መረብ አገናኝቶ ሀላባ ከተማን መሪ ማድርግ ችሎ ነበር።

ሆኖም ግን ሀላባዎች በመሪነት የቆዩት ለስምንት ደቂቃ ብቻ ነበር። በ64ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ በለጠ ከመሃል ሜዳ አከባቢ በረጅሙ ያሻማውን ኳስ ሀሰን ሁሴን በግንባሩ ገጭቶ አሻግሮለት ሙሉቀን ተሾመ ወደግብነት ቀይሮ ጨዋታው አንድ እኩል እንዲሆን ሆኗል። አቻ ከሆኑ በኋላ ጨዋታው ግለቱ እየጨመረ ሁለቱም ቡድኖች በመነቃቃት ተጫውተዋል። እንዲሁም በርከት ያለ የግብ ሙከራም አድርገዋል። በ69ኛው ደቂቃ የቤንች ማጅ ቡናው ናትናኤል ዳንኤል ከሙሉቀን ተሾመ ጋር በአንድ ለአንድ ቅብብል ከግብ ክልል ውጪ ሆኖ አክርሮ የመታትን ኳስ የግብ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ትታወሳለች። መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ አልቆ ተጨማሪ ሲታይ ቤንች ማጅ ቡናዎች የመጨረሻ ዕድል አግኝተው በ90+2 ላይ በአብዱላዚዝ አማን አማካኝነት ግብ አስቆጥረው 2ለ1 በሆነ ውጤት በማሻነፍ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።

ቀን 10:00 ላይ ነቀምቴ ከተማን ከይርጋጨፌ ቡና ያገናኘው መርሃግብር በነቀምቴ ከተማ በላይነት ተጠናቋል።

የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት ይርጋጨፌ ቡናዎች  ጨዋታው ከመጀመሩ ገና በ3ኛው ደቂቃ የይርጋጨፌ ቡናው መላአልኤል ርቀት ላይ ሆኖ በመምታት ግሩም ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ቀዳሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በ11ኛው ደቂቃ የነቀምቴ ከተማው ኢብሳ በፍቃዱ መሰመር ላይ የመታትን ኳስ የይርጋጨፌ ቡናው ግብ ጠባቂ ኳስ የወጣ መስሎት ሲዘናጋ ወደግብነት ተቀይራ አንድ እኩል እንዲሆኑ ሆኗል።

የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ነቀምቴዎች ወደጨዋታ በመመለስ ተወስዶባቸው የነበረውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በማስመለስ ተጨመሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። ይርጋጨፌ ቡና በአንፃሩ እንቅስቃሴያቸውን እየተዳከመ መጥቷል። ይሄንን አጋጣሚ የተጠቀሙት ነቀምቴዎች በ26ኛው ደቂቃ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። ሠለሞን ጌታቸው ከመሃል ሜዳ አከባቢ  የሰነጠቀለት ኳስ ታረቀኝ ታደሰ ይዞ በመግባት  ከመረብ ጋር አገናኝቷል። የመጀመሪያው አጋማሽም በነቀምቴ ከተማ 2ለ1 መሪነት ተጠናቆ ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ነቀምቴ ከተማዎች ፍፁም የጨዋታ በላይነት ወሰደው ተጨማሪ ግቦችንም አስቆጥረዋል። ከእረፍት መልስ በ53ኛው ደቂቃ ሠለሞን ጌታቸው በራሱ ጥረት ግብ የይርጋጨፌ ቡናን ተከታዮች እና ግብ ጠባቂ አታሎ በማለፍ ሦስተኛውን ግብ ለነቀምቴ ከተማ አክሏል። እንዲሁም ተመስገን ዱባ 64ኛው ደቂቃ በግሩም አጨራረሰ አራተኛውን ግብ ከመረብ ጋር ከገናኝቶ መሪነታተውን አስፍቷል። በሌላኘው ወገን በ81ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው የአብስራ ወርቅነህ ሁለተኛ ግብ ለይርጋጨፌ ቡና አስቆጥሮ ወደጨዋታ እንዲመለሱ አድርጓል።

ሆኖም ግን መደበኛ የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየ ደቂቃ ውስጥ 90+2 ላይ ተቀይሮ የገባው ሱልጣን አብይ 5ኛ ግብ ለነቀምቴ ከተማ አስቆጥሮ ጨዋታውን ወደመጨረስ ሲያደርግ በ90+4 ላይ ገመቺሳ አማኑኤል በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል በዚህም ጨዋታው 5ለ2 በሆነ ውጤት በነቀምቴ ከተማ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ሆኗል።