መረጃዎች | 78ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት መርሃግብር ነገ ጅማሮውን የሚያደርግባቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከወላይታ ድቻ

የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ መርሃግብር ሁለቱን ድል ተራቡ ቡድኖችን የሚያገናኝ ይሆናል።

በ12 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልቂጤ ከተማዎች በሊጉ ለመቆየት ለአስራ አንድ ሳምንታት ከራቃቸው ድል ጋር መታረቅ ግድ ይላቸዋል።

ሰራተኞቹ ከተከታታይ ሽንፈቶች ተላቀው በ2 ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ተካፍለው ከመውጣት በዘለለ በእንቅስቃሴ ረገድም መሻሻሎች አሳይተዋል።ቡድኑ በተከታታይ ሳምንታት ካሳካው ነጥብ በተጨማሪ በጨዋታዎቹ ግቡን ሳያስደፍር መውጣቱ እንደ አንድ በጎ ጎን የሚታይ ቢሆንም በፊት መስመሩ ላይ ያለው ትልቅ ድክመት ግን የቡድኑ መሻሻል በውጤት እንዳይታጀብ አግዶታል።

ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ ድል ካደረገበት ወቅት በኋላ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ላይ ማስቆጠር የቻለው የግብ መጠን 2 ብቻ ነው፤ ይህም የፊት መስመሩ የስልነት ደረጃ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። በሁነኛ አጥቂ ችግር ምክንያት ተመስገን በጅሮንድን በፊት መስመር ለማሰለፍ የተገደዱት አሰልጣኝ ሙልጌታ ምህረት ተጨማሪ የግብ ምንጭ ፍለጋ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

በሊጉ ሙሉ ሶስት ነጥብ ካሳኩ ስድስት ጨዋታ ያስቆጠሩት ወላይታ ድቻዎች በ24 ነጥቦች በ11ኛ የሚገኙ ሲሆን በተከታታይ ጨዋታዎች የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾች የሆኑትን አንተነህ ጉግሳ እና ቢኒያም ፍቅሬን በቀይ ካርድ ማጣታቸው ቡድኑን በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ተዳክሞ እንዲቀርብ ያስገደዳቸው ይመስላል።

በመጀመሪያው ዙር በሊጉ የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያስመለክት የነበረውን ቡድን ወደ መስመር የመመለስ ኃላፊነት የአሰልጠኝ ያሬድ ገመቹ ቀዳሚ የቤት ስራ ይመስላል ፤ በተለይ በሊጉ እምብዛም የመጫወት ልምድ በሌላቸው ተጫዋቾች የተገነባው ቡድኑ በጨዋታዎች ወሳኝ ቅፅበቶች ላይ ጨዋታዎችን በመቆጣጠር ረገድ የሚስተዋልበትን ክፍተት መድፈን የግድ ይላቸዋል።

በወላይታ ድቻዎች በኩል ቅጣት ላይ ከሚገኙት አንተነህ ጉግሳ እና ቢኒያም ፍቅሬ ውጭ የተቀረው ስብስብ ለነገ ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ መሆናቸው ሲታወቅ በአንፃሩ በወልቂጤ ከተማዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ነገር ግን የክለቡ እግድ መነሳቱን ተከትሎ ከክለቡ ጋር ልምምድ ሲሰሩ የቆዩ ተጫዋቾች በነገው ጨዋታ የሚሳተፉበት ዕድል እንዳለ በጭምጭምታ ደረጃ ሰምተናል።

ወላይታ ድቻ እና ወልቂጤ 7 ጊዜ ተገናኝተው ወልቂጤ ከተማ 3 ሲያሸንፍ ወላይታ ድቻ 2 ጊዜ አሸንፈዋል ቀሪዎቹ 2 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ። በዚህም ወልቂጤ 7 ሲያስቆጥር ድቻ 5 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀምበሪቾ

የምሽቱ መርሃግብር ደግሞ በሰንጠረዡ ሁለት ፅንፍ የሚገኙትን ቡድኖች የሚያገናኝ ጨዋታ ይሆናል።

በሰንጠረዡ 37 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በመጨረሻ 3 የሊግ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው 9 ነጥቦች 2 ብቻ በማሳካት ከተከታዩቻቸው ልቀው በሰንጠረዡ አናት ሊቀመጡ የሚችሉበትን ዕድል አምክነዋል።

በብዙ መልኩ በቀደመው የብቃት ደረጃቸው ላይ የማይገኘቱ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተከታታይ ጨዋታዎች ከውጤት ማጣታቸው ባለፈ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው በብዙ መልኩ መሻሻልን የሚሻ ነው ፤ በተለይ ደግሞ የቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ በብዙ መልኩ ማደግ የሚገባው ስለመሆኑ እያስተዋልን እንገኛለን።

የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ስብስብ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የመቆየት ተስፋውን ለማስቀጠል በቀጣይ ነጥቦችን በመጣላቸው የሚቀጥሉ ከሆነ በፉክክር ውስጥ የመቀጠላቸው ጉዳይ እየጠበበ የሚመጣ በመሆኑ በቀጣይ የሚኖሩትን ጨዋታዎች በትኩረት ማድረግ የግድ ይላቸዋል።

በሊጉ የመቆየት ህልማቸውን እውን ለማድረግ ጊዜ እየረፈደባቸው የሚገኙት ሀምበሪቾዎች ከዚህ በኃላ የሚያደርጓቸው 11 የሊግ ጨዋታዎች ለእነሱ ከፍፃሜ ጨዋታ በላይ ዋጋ ያላቸው ይሆናሉ።

ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ያለባቸውን የ8 ነጥብ ልዩነት የማስወገድ ከፍተኛ የቤት ስራ የሚጠብቀው ቡድኑ ከዚህ በኃላ ተጨማሪ ጨዋታዎችን መሸነፍ ማለት ወደ ወራጅነት ራሳቸውን ይበልጥ የሚያቀርብ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ ተጋድሎ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በረከት ግዛቸው በቅጣት እንዲሁም ብሩክ እንዳለ ደግሞ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በሀምብሪቾ በኩል ቀለል ያለ ጉዳት አጋጥሞት በነገው ጨዋታ መሰለፉ አጠራጣሪ ከሆነው ምናሴ ቢራቱ ውጭ ሙሉ ቡድን ለጨዋታው ዝግጁ ነው።