የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን አጠናክሯል

በ11ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ተደርገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን ሲያጠናክር አርባምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማም አሸንፈዋል።

ረፋድ 3:00 አዳማ ከተማን ከአርባምንጭ ከተማ ያገናኘው መርሃ ግብር በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረ ብቸኛ ግብ አርባምንጭ ከተማን አሸናፊ አድርጓል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት አርባምንጭ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ቢሆኑም ግብ ማስቆጠር የሚችሉበትን ያለቁ ኳሶችን አግኝተው በደካማ አጨራረስ ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ተስተውለዋል። አዳማ ከተማዎችም ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶችን ማግኘች የቻሉ በሆንም ጥሩ የነበረውን የአርባምንጭ ከተማን የኋላ መስመር አለፈው ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በተደጋጋሚ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አግኝተው ሳይጠቀሙ ሲቀሩ የነበሩት አርባምንጮች በ11ኛው ደቂቃ ትውፊት ካዲዬ ከመሰመር አከባቢ ያሻገረችውን ኳስ ሰርካለም ባሣ በቀላሉ ስትመታ የአዳማ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ለመመለስ ጥረት ብታደርግም በእጆቿ መካከል ገብታ አርባምንጮችን መሪ አድርጋ ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ቀዝቀዝ ያለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለተመልካች አስመለክተዋል። አዳማ ከተማ ይባስ የተዳከሙበትን ሁለተኛ አጋማሽ ሲያሳልፋ አርባምንጭ ከተማም በኳስ ቁጥጥር ጥሩ ቢሆኑም ግብ ለማስቆጠር የተቸገሩበትን ሁለተኛ አጋማሽ አሳልፈዋል። የአርባምንጭ ከተማዋ የፊት መስመር ተጫዋች በሆነቸው በሰርካለም ባሳ ላይ መድረሻቸውን ያደረጉ ረጃጅም እና የአንድ ለአንድ ቅብብል ኳሶች ወደፊት ቢጣሉም ሰርካለም ባሳ በደካማ አጨራረስ ሳትጠቀም ስትቀር ለመመልከት ተችሏል። በዚህም ደካማ እንቅሰቃሴ ያስመለከተው ሁለተኛ አጋማሽ ለመጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀሩት የአርባምንጭ ከተማዋ ግብ ጠባቂ የመልስ ምት መምታት ዘግይታለች በሚል ምክንያት 88ኛ ደቂቃ ላይ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ የቀይ ካርድ ሰላባ ሆና ከሜዳ ተሰናብታለች። በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ በሰርካለም ባሣ አማካኝነት በተቆጠረው ብቸኛ ግብ አርባምንጭ ከተማ በጠባብ ውጤት ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

ቀን 8:00 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከልደታ ክፍለ ከተማ ያገናኘው መርሃ ግብር በንግድ ባንክ በላይነት ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቁጥጥር ተሽለው በመገኘት ተቂራኒ ቡድን ላይ ጫና አሳድረው የግብ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የመጀመሪያዎቹን 40 ደቂቃዎች ጠንካራ የነበረውን የልደታን ተከላካይ መሰመር አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ልደታ ክፍለከተማም  በአንፃሩ የመጀመሪያው ግብ እስኪያስናግዱ ድረስ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ለመሆን በመልሶ ማጥቃት አንዳንድ ኳሶችን አግኝተው በደካማ አጨራረስ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ሰንብተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቁ ደቂቃዎች ሲቀሩት በ43ኛው ደቂቃ እመቤት አዲሱ ከማዕዘን ምት ያሻማችውን ኳስ የልደታዋ ግብ ጠባቂ ለመመለስ ጥረት ስታደርግ አምልጧት ከመረብ ጋር ተገናኝቶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 እየመራ ወደመልበሻ ክፍል እንዲገቡ ሆኗል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የተጫዋች ቅያሪ አድርገው በጫና ገብተዋል። ልደታዎችም የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጠንከር ብለው ሲጫወቱ ለመመከት ተችሏል። ሁለቱም ቡድኖች ኳስ መስርተው ግብ ለማስቆጠር  ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ግን ንግድ ባንክ ተጨማሪ ግብ በማስቆጠር የኳስ ብልጫ ወስዷል። ተቀይራ የገባችው አረጋሽ ካልሳ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ በ71ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ ለንግድ ባንክ አስቆጥራ መሪነታቸውን በማስፋት ጨዋታው ወደመገባደጃው እንዲሄድ አስችላለች። ንግድ ባንክ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በጫና ቢጫወትም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 2ለ0 በሆነ ውጤት በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተገባዷል።

የዕለቱ ሦሰተኛ መርሀግብር አዲስ አበባ ከተማን ከሀዋሳ ከተማ አገናኝቶ ሀዋሳ ከተማ በሰፊ ግብ ልዩነት አሸንፏል።

ሁለቱም ጥሩ የጨዋታ እንቅስሴ ባስመለከቱበት በአስር ሰዓቱ ጨዋታ ከበርካታ ሀዋሳ ተመልካች ጋር ታጅቦ ማራኪ የኳስ አጨዋወት ታይቶበታል። የመጀመሪያው ግብ እስቆጠር ድረስ በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች በሁለቱም ቡድኖች መካከል ተደርጓል። በተለይም ሀዋሳ ከተማ በርከት ያለ ግብ ማስቆጠር ሚችልበትን አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀም ቀርቷል። በ26ኛው ደቂቃ ሀዋሳዎች ኳስ ይዘው በሚገቡበት ወቅት የአዲስ አበባ ተጫዋቾች ባደረጉት የእጅ ንክኪ ፍፁም ቅጣት ምት ለሀዋሳ ከተማ ተሰጥቷቸዋል። እሙሽ ድንኤል በመምታት ወደ ግብነት ቀይራ ሀዋሳ ከተማን መሪ አድርጋ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲቀጥል አዲስ አበባ ከተማ ወደ ፊት ገፍቶ ተጫውቷል። ሀዋሳ በከተማም አንዳንድ የግብ ሙከራ ያደረገ ሲሆን አደገኛ ሙከራ በ50ኛው ደቂቃ እፀገነት ግርማ ከእሙሽ ዳንኤል ጋር አንድ ለአንድ ቅብብል በማድረግ የመታቸው ኳስ የግብ አግዳሚ መልሶባታል። ምንም እንኳን በኳስ ቁጥጥር ቢበለጡም ሀዋሳ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በ77ኛው ደቂቃ እሙሽ ዳንኤል በመስመር በኩል ኳስ ይዛ በመግባት ወደግብ መጥታ የአዲስ አበባዋ ግብ ጠባቂ ለመያዝ ሲትሞክር ኳስ ነጥሮባት ወደግብነት ተቀይሮ ሀዋሳ ከተማ መሪነቱ አስፍቷል። ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ አዲስ አበባ ከተማዎች መዘናጋት ታይቶባቸዋል። ይህንን ክፍተት የተጠቀሙት ሀዋሳዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሁለት ደቂቃ ብቻ ፈጅቶባቸዋል። በ79ኛው ደቂቃ ላይ ረዲኤት አስረሳኸኝ በመሰመር በኩል ኳስ ይዛ በመግባት ጨርሳ ያቃበለቻት ኳስ ተመቻችታ ሲትጠባበቅ የነበረቸው ሰለማዊት ጎሳዬ ሦስተኛ ግብ አክላ ጨዋታው በሀዋሳ ሦስት ለምንን አሸናፊነት ተጠናቋል።