ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና በመጨረሻ ደቂቃ ድራማ ታጅቦ ሀዋሳን ድል አድርጓል

ጥሩ ፉክክር በተደረገበት የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ ድራማዊ ጎሎች ታግዞ  ኢትዮጵያ ቡና ሀዋሳ ከተማን 3-2 አሸንፏል።

ኢትዮጵያ ቡና በፋሲሉ ጨዋታ የተጠቀመውን ቋሚ አሰላለፍ ለውጥ ሳያደርጉ ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ ከመድኑ የአቻ ውጤት አንፃር ሀዋሳ ከተማ ቅጣት ባስተናገደው በረከት ሳሙኤል ሰለሞን ወዴሳን ፣ ጉዳት በገጠመው አማኑኤል ጎበና ቦታ አቤኔዘር ዮሐንስን እንዲሁም ሲሳይ ጋቾን ከቅጣት በተመለሰው እንየው ካሳሁን ተክተዋል።

ጠንከር ባለ ዝናብ ታጅቦ ሁለቱን የሊጉ ዕድሜ ጠገብ ክለቦችን ያገናኘው ጨዋታ ጎልን ያስመለከተን ገና 3ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የሀዋሳ ከተማው የግብ ዘብ ፂሆን መርዕድ ከራስ ሜዳ በአግባቡ ያላራቃትን ኳስ አብዱልከሪም ወርቁ ከተቆጣጠራት በኋላ ወደ ግብ ያሻገረለትን ኳስ የሠለሞን ወዴሳ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት መስፍን ታፈሠ ከጀርባ ሆኖ ያገኛትን ኳስ  የልጅነት ክለቡ መረብ ውስጥ አዋህዷታል። ሀዋሳዎች ከታፈሰ እግር ስር በሚነሱ ኳሶች አሊ ሱለይማንን የማጥቂያ መነሻ በማድረግ በሰንጣቂ እና ተሻጋሪ ኳሶች እንቅስቃሴ ወደ አቻነት ለመምጣት ጥረት ማድረግ ቢችሉም ቡድኑ በተቃራኒው በቅብብል ወቅት የሚፈጥሯቸው ስህተቶች በተደጋጋሚ በቡና ተጫዋቾች ይቋረጡ ስለነበር ለኢትዮጵያ ቡና የሽግግር አጨዋወት በእጅጉ ምቹ አቀራረብ ነበረው።

ጨዋታው 18ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ ሀዋሳዎች  በጥሩ ቅብብል ታፈሰ የሰጠውን አሊ ከአቤኔዘር ጋር ተቀባብሎ አቤኔዘር በመጨረሻም መልካሟን  አጋጣሚን ሳይጠቀምባት ቀርቷል። 27ኛው ደቂቃም ላይ እዮብ ከግራ ወደ መሐል ገባ ብሎ  በተከላካዮች መሐል አሾልኮ የሰጠውን አሊ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከግቡ ትይዩ ተገኝቶ የመታትን ኳስ በረከት አማረ በጥሩ ብልጠት ከጎልነት ኳሷን አግዷታል። ከራስ ሜዳ በንክኪ በመውጣት በመስመር በኩል የሰሉ ጥቃቶችን በመሰንዘሩ ረገድ የተዋጣላቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች የግብ መጠናቸው ከፍ ያደረጉበትን ግብ አክለዋል። 34ኛው ደቂቃ ከማዕዘን መነሻዋን ያደረገችን ኳስ አብዱልከሪም ወደ ሳጥን ሲያሻግር ግብ ጠባቂው  ፂሆን መርዕድ የመለሳት ኳስ መስፍን ታፈሠ እግር ስር ደርሳ አጥቂው ከሳጥን ውጪ ያገኛትን ኳስ አክርሮ በመምታት በጨዋታው ሁለተኛ በደርሶ መልስ አራተኛ ግቡን በቀደመ ክለቡ መረብ ላይ አስቆጥሯል።

ቡናማዎቹ የሀዋሳን ስህተት ለመጠቀም የሚያደርጉትን ጥረት በይበልጥ ቀጥለው በአማኑኤል አድማሱ አማካኝነት አከታትለው ሁለት ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይ 40ኛው ደቂቃ በፍቃዱ በጥሩ እግር ስር ከቀኝ ወደ ውስጥ ያሻገራትን አማኑኤል አድማሱ ነፃ ቦታ ሆኖ የመታት  ኳስ የግቡን ቋሚ ብረት ታካ ልትወጣ ችላለች። በአጋማሹ በተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች ሀዋሳዎች ከቆሙ ኳሶች ወደ ጨዋታ ለመመለስ በድግግሞሽ  ጥረት ቢያደርጉም በ2ለ0 የኢትዮጵያ ቡና መሪነት ጨዋታው ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ጥንቃቄ አዘል አጨዋወቶች የተበራከቱበት ሲሆን አጋማሹ እንደተጀመረም ቡናማዎቹ በአንተነህ ተፈራ አማካኝነት ፈጣን ሙከራን ካደረጉ ከአንድ ደቂቃ በኋላም 46ኛው ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት አብዱልከሪም ያቀበለውን ኳስ መስፍን ታፈሠ ሦስተኛ ግብ ልትሆን የምትችለዋን ግብ በፂሆን መርዕድ መክኖበታል።

መጠነኛ መቀዛቀዞች  በጨዋታው እንመልከት እንጂ ኳስን ሲያገኙ ሽግግሮቻቸው አደገኛ የነበሩት የአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ልጆች 59ኛው ደቂቃ ከእጅ ውርወራ እንየው ወደ ኋላ ለፀጋአብ ሲጥልለት በመሐል አማኑኤል ያገኛትን ኳስ በግራ አግዳሚው ሰዷታል። ከመጀመሪያው አጋማሽ አኮያ የማጥቂያ መንገዳቸው በእጅጉ የሳሳባቸው ሀዋሳዎች በቅያሪ ተጫዋቾችም ጭምር ዕድሳት ለማድረግ ቢሞክሩም ቡድኑ ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲገባ በቁጥር ስለሚያንሱ ለቡና ተከላካዮች በቀላሉ ተጋላጭ ነበሩ።

ሀዋሳዎች 63ኛው ደቂቃ አሊ ከአቤኔዘር ያገኘውን ኳስ መሬት ለመሬት ወደ ውስጥ ሲያሻግር ዋሳዋ ያወጣበት እና ከአንድ ደቂቃ መልስም አሊ በግራ የሰጠውን አቤኔዘር መቶት በረከት አድኖበታል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል በተደረገ ሙከራ  አብዱልከሪም በግል ጥረቱ ወደ ሳጥን እየነዳ ገብቶ የሞከራትን ፂሆን የመለሰበት እና 72ኛው ደቂቃ ላይ ጣጣዋን የጨረሰች ኳስ አብዱልከሪም ሰጥቶት አንተነህ ብረት ከመለሰበት ሙከራ መልስ የጨዋታውን የመጨረሻ ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማዎች ተጫዋቾችንም ጭምር በመለወጥ ጫና መፍጠርን በጀመሩበት ቅፅበት ወደ ጨወታ የመለሳቸውን ግብ አሳክተዋል።

82ኛው ደቂቃ ከግራ የሜዳ ክፍል ከእጅ ውርወራ እንየው የሰጠውን አሊ ወደ ግብ ክልል ሲያሻግር ተቀይሮ የገባው እስራኤል እሸቱ በመጀመሪያ ንክኪው ኳሷን ወደ ጎልነት ለውጧታል። ወደ አቻነት ለመምጣት በትጋት የታተሩት ሀዋሳዎች 90+3 እንየው ወደ ግብ ያሻማውን ኳስን ግብ ጠባቂው በረከት መቆጣጠር ተስኖት አብዱልባሲጥ በግንባር ወደ ግብነት ቀይሯታል። ከጎሏ በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ከማዕዘን ምት ከተደረጉ የጥቃት መነሻዎች በኋላ ኢትዮጵያ ቡና የአሸናፊነት ጎላቸውን አግኝተዋል። ከማዕዘን ተሻምቶ ዋሳዋ በግንባር ገጭቶ ፂዮን መልሷት በድጋሚ ወጥታ ወደ ማዕዘን ምትነት የተለወጠችን ኳስ በፍቃዱ አሻምቶ ራምኬል ጀምስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር በጭማሪ ደቂቃ ድራማዎች ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 3ለ2 ድል አድራጊነት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀዋሳው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ አጀማመራቸው ላይ ስህተት ስለነበር ጎሎችን እንዳስተናገዱ ተናግረው ከዕረፍት በኋላ ግን ቡድናቸው ተስተካክሎ እንደነበር እና ነገር ግን ለማስቆጠር መቸገራቸውን ገልፀው በመጨረሻ ደቂቃዎች ግን ኢትዮጵያ ቡና ያገባል ብለው ተጫዋቾቻቸውን አለማሰባቸውን ተከትሎ ጎል  እንደተቆጠረባቸው ጠቁመው ተጋጣሚያቸው  ዕድለኛ እንደነበርም ጭምር ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በበኩላቸው ብዙ የጎል አጋጣሚ ፈጥረው አለመጠቀማቸው ይህ ውጤት ባይመዘገብ ያስቆጭ እንደነበር ጠቁመው  የተወሰነ የዕብደት ሰዓት ስለነበረ ጎል ተቆጥሮባቸው አቻ ሊለያዩ ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ፈጣሪ ፈቅዶ ጎል አስቆጥረን ማሸነፋችን አስደስቶኛል ሲሉ ተደምጠዋል።