ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ደሴ እና ባቱ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት የመርሐ ግብር ሽግሽግ ተደርጎ ዛሬ መከናወን ጀምረው ደሴ ከተማ እና ባቱ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን ሲያሸንፉ ኦሜድላ እና ጋሞ ጨንቻ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ በደሴ ከተማ እና ባቱ ከተማ መካከል ተከናውኖ ደሴ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠረ ግብ 1-0 አሸንፏል።


በመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በኳስ ቁጥጥር እና በሙከራ በአንፃራዊነት የተሻሉ የነበሩት ደሴዎች መሪ ሊሆኑባቸው የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ በሱፍቃድ ያሻገረው ኳስ የኋላሸት ፍቃዱን ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት ቢያገናኘውም የመታው ኳስ ወደ ውጪ ሲወጣበት 18ኛው ደቂቃ ላይ በረጃጅም ኳሶች ወደ ተቃራኒ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ካፋዎች ኃይሌ እሸቱ በግል ጥረቱ ወደ ግብ ይዞ በመሄድ ሙከራ አድርገው ወደ ውጪ ወጥቷል። ደሴዎች ይሄንኑ ኳስ በመልስ ምት ከራሳቸው የግብ ክልል በጥሩ ሁኔታ መስርተው በመሄድ በመጨረሻ የኋላሸት መትቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። 38ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻማውን ኳስ ዘሪሁን ሞክሮ በግቡ አግዳሚ ለጥቂት የወጣበት ሙከራም በደሴ በኩል ሌላው የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ካፋዎች በተሻለ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ቢሆንም በጎል ሙከራዎች ማጀብ ያልቻሉ ሲሆን አሁንም በግብ ሙከራ የተሻሉ የነበሩት ደሴዎች ነበሩ። 76ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ብርሃኑ ከመስመር የመጣውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ሲወጣበት 85ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አቡሽ ደርቤ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በደሴ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሸገር ከተማን ከባቱ ከተማ ባገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ባቱዎች ከዕረፍት መልስ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 3-0 አሸንፈው ወጥተዋል።

በመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት ሸገሮች ሙከራዎች ቢያደርጉም የጨዋታው ኮከብ ሆኖ በዋለው የባቱው ግብ ጠባቂ ኢያሱ ተካ ጥረት ግብ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በተለይ 8ኛው ፣ 28ኛው እና 30ኛው ደቂቃዎች ላይ ሸገሮች ያደረጓቸውን ጠንካራ ሙከራዎች በግሩም ሁኔታ ማዳን ችሏል።

ከዕረፍት በኋላ ባቱዎች የተጫዋች ለውጦች በማድረግ የበላይነቱን ወስደው መጫወት የቻሉ ሲሆን በተለይ በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ላይ ውጤታማ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ድል መጨበጥ ችለዋል። 71ኛው ደቂቃ ላይ እስራኤል ሻጎሌ በመስመር በኩል ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሲልከው የግብ ጠባቂው መዘናጋት ታክሎበት ወደ ግብነት ሲቀየር 78ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ሀቢብ ጃለቶ በቀጥታ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ሲተፋው በቅርብ ርቀት የነበረው አስጨናቂ ዲሮ አስቆጥሮ ልዩነቱን አስፍቷል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሸገሮች ለማጥቃት በሄዱበት ቅፅበት በረጅሙ የተጣለውን ኳስ አማኑኤል ተፈራ ከተከላካዮች አምልጦ ግብ ጠባቂውን በማለፍ ሦስተኛውን ጎል በጥሩ አጨራረስ አስቋጥሮ ጨዋታው በባቱ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተደምድሟል።

በዕለቱ የመዝጊያ መርሐግብር ጋሞ ጨንቻ እና ኦሜድላ ተገናኝተው አንድ አቻ ተለያይተዋል።


ሳቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ እምብዛም የጎል ዕድሎች ያልፈጠሩ ሲሆን ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን የቻሉት ጨንቻዎች ናቸው። 27ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ መኮንን በራሱ ጥረት ያገኛትን ኳስ ወደ ግብነት ለውጦ ቡድኑን
መሪ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስም እንደመጀመርያው አጋማሽ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ያልታየበት ሲሆን 71ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥን ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አስቻለው ኡታ በአግባቡ በመጠቀም ኦሜድላን አቻ አድርጓል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ዳግም ግርማ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሯል። ይህም ውዝግብ የፈጠረ ክስተት ሆኖ ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።