ከፍተኛ ሊግ ምደብ ሀ | ሀላባ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ድል ቀንቷቸዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ”ሀ” 19ኛው ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ጅማሮውን አድርጎ ሀላባ ከተማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን ሲያሸንፉ ቤንች ማጂ ቡና እና ነቀምቴ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ረፋድ 3:00 ጅማሮውን ያደረገው መርሐግብር ቤንች ማጂ ቡናን ከነቀምቴ ከተማ አገናኝቶ በሁለቱም አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ነጥብ አጋርቶ ተጠናቋል።

ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ኳስን ወደፊት ይዞ በመግባት ግብ ለማስቆጠር ከመሞከር ይልቅ ወደ ኋላ መለስ በማለት የተጫወቱበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አስመልክተዋል። በተለይም ቤንች ማጂ ቡናዎች ኳስን ወደኋላ በመመለስ በራሳቸው ሜዳ በመጫወት በኳስ ንክኪ ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ቢያደርጉም እምብዛም የግብ ሙከራ አላደረጉም። ነቀምቴ ከተማ በአንፃሩ ቶሎ ቶሎ ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ለመግባት ጥረት ያደረገ ቡድን ነበር። በ37ኛው ደቂቃ የነቀምቴ ተከላካይ ርሆቦት ሰላሎ ጃፋር ሙድሰር ላይ በሠራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ለቤንች ማጂ ቡና ተሰጥቶ አብዱልአዚዝ አማን ከመረብ ጋር አገናኝቶ ቤንች ማጅ ቡናዎች እየመሩ የመጀመሪያውን አጋማሽ እንዲያገባድዱ አድርጓል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ነቀምቴ ከተማ ጠንከር ብሎ በመግባት በጫና ሲጫወቱ በርከት ያለ የግብ ሙከራም አድርገዋል። እንዲሁም በኳስ ቁጥጥር በልጠው ጠንከር ያለ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም የቤንች ማጂው ግብ ጠባቂ ናትናኤል ተፈራ በግሩም ሁኔታ ኳሶችን ሲመልስባቸው ለመመለከት ተችሏል። ቤንች ማጂ ቡና በሁለተኛው አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሳይሆን ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደኋላ አፈግፍጓ ሲጫወት ተስተውለዋል። በዚህም ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ እስኪቀራቸው ድረስ በመከላከሉ ረገድ ስኬታማ ነበሩ። ሆኖም ግን በ86ኛው ደቂቃ ግባቸውን ለማስደፈር ተገደዋል። በ86ኛው ደቂቃ ረጅሙ ተከላካይ ርሆቦት ሰላሎ ከመሰመር የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ቀን 8 ሰዓት ላይ ሞጆ ከተማን ከሀላባ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በወሰን ጌታቸው ብቸኛ ግብ ሀላባ ከተማን አሸናፊ አድርጓል።

ማራኪ የጨዋታ እንቅሰቃሴ ባስመለከተው በዚህ መርሐግብር ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ቶሎ ቶሎ ወደተቃራኒ ቡድን እየገቡ የግብ ሙከራ ከጥሩ ኳስ ቁጥጥር ጋር አድርገዋል። በርከት ያሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን የፈጠሩት ሁለቱም ቡድኖች አስቆጪ የሚባሉ አጋጣሚዎችንም ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ተስተውለዋል። አጋጣሚውን በመጠቀም ኳስና መረብ በማገናኘት ሀላባ ቀዳሚ ነበር። በ27ኛው ደቂቃ የሀላባ ከተማው ወሰን ጌታቸው ከመስመር የተሻማውን ኳስ አየር ላይ እያለ በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ በማሳረፍ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ አድርጓቸዋል። ግብ ተቆጥሮባቸው የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በጫና የተጫወቱት ሞጆዎች ብልጫ የወሰዱ ቢሆንም ሀላባዎች ወደኋላ አፈግፍገው በመጫወታቸው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ሞጆ ከተማ ፍፁም የጨዋታ በላይነት ከኳስ ቁጥጥር ጋር መውሰድ ችሏል። ሀላባ ከተማ በአንፃሩ ውጤቱን ለማስጠበቅ ሲከላከሉ ተስተውለዋል። አልፈው አልፈውም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። ሞጆ ከተማ አንዳንድ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጨዋታው ወደ አንድ ጎን እንዲይዝ አድርገዋል። የሞጆው ዮናታን ግርማ ኳሶችን ከመሃል ይዞ በመግባት በተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል። ሆኖም ግን ጨዋታው ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክት በወሰን ጌታቸው ብቸኛ ግብ ሀላባ ከተማን አሸናፊ በማድረግ ተገባዷል።


ቀጥሎ 10:00 ላይ የተደረገው ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማን ከጅማ አባ ቡና አገናኝቶ በኮልፌ የበላይነት ተጠናቋል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም የግብ ማግባት ሙከራ ሲያድርጉ አልተስተዋለም። ቢሆንም ኮልፌ ቀራኒዮ አልፎ አልፎ ኳስ ተቆጣጥረው ወደ ተቀራኒ ቡድን ክልል በመግባት ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን ፈጥሮ በደካማ አጨራረስ ሳይጠቀም ቀርቷል። ጅማ አባ ቡናም በአንፃሩ ኳስ መስርተው እና ተረጋግተው ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ወደተጋጣሚው ቡድን ግብ ክልል መግባት ተስኗቸው የመጀመሪያ አጋማሽ ለማሳለፍ ተገደዋል። ምንም እንኳን በኳስ ቁጥጥር እና ንክኪ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ቢሆንም የግብ ማግባት ሙከራ ደካማ የሆኑበት አርባ አምስት በማሳለፍ አንደኛው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ  ጨዋታው ሲመለስ ኮልፌዎች ጠንከር ብለው መመለስ ሲችሉ ጅማ አባ ቡናም በአንፃሩ ከመጀመሪያው አጋማሽ ደከም ያሉበትን እንቅስቃሴ አስመልክተዋል። ይሄንን ያስተዋሉት ኮልፌዎች ኳስ ወደፊት ይዘው ሲገቡ ተስተውለዋል። በዚህም ኳስና መረብ በማገናኘት ቀዳሚ ሆነዋል። በ60ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስ አግኝተው ማቆያ አልታየ ቀጥታ ወደግብ ሲመታት የአባቡናዎቹ ግብ ጠባቂ ጥረት ቢያደርግም ኳሷ አምልጣው ከመረብ ጋር ተገናኝታ ኮልፌዎችን መሪ አድርጋለች። ግብ ከተቆጠረ በኋላ ጨዋታው ግለቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን አባቡናዎች የጨዋታ ብልጫ ወስደው የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫና አሳድረዋል። ኮልፌዎች በአንፃሩ ወደኋላ በመመለስ በጥሩ ሁኔታ ተከላክለዋል። በዚህም አባቡናዎች ግብ ለማስቆጠር ተቸግረው ጨዋታውም በኮልፌ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።