ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | የ19ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 19ኛው ሳምንት በሁለተኛ ቀን ዛሬ ቀጥሎ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ሲገባደድ ተጠባቂው የንብ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቆ አዲስ አበባ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና ኦሮሚያ ፖሊስ አሸንፈዋል።


ረፋድ ሦስት ሰዓት ሲል የጀመረው ተጠባቂው ንብን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቶ ያለግብ ተጠናቋል። ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባስመለከተው በመጀመሪያው አጋማሽ በቡድኖቹ መካከል ጥሩ ሚባል የኳስ ቁጥጥር ታይቷል። ኤሌክትሪክ በማጥቃት ረገድ ብልጫ የወሰደ ቡድን ሆኗል። ንብ በአንፃሩ ኳስ መስርቶ መጫወት ቢችልም ወደፊት የመሄድ ጉዟቸውን የኤሌክትሪክ ተከላካዮች በአጭሩ ሲያጨናግፉ ተስተውሏል። ምንም እንኳን ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ እና በተደጋጋሚ ወደ ግብ የሚደርሱ ኳሶችን መመልከት ቢቻልም ግብ መሆን ሚችሉ አደገኛ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አልተስተዋሉም።

በሁለተኛው አጋማሽም ጨዋታው ጥንካሬውን ጨምሮ ሲመለስ ንብ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መሄድ የቻለበትን ሁለተኛ አርባአምስት አሳልፏል። ኤሌክትሪክም አልፈው አለፈው በሚያደርጉት የግብ ማግባት ሙከራ የንብ ተከላካዮች በደንብ በመከላከል አጋጣሚዎቹን እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል። አደገኛ የሚባለውን ሙከራ የንቡ ታምራት ስላስ በ70ኛው ደቂቃ ሲያደርግ በመስመር በኩል ኳሰ ይዞ በመሄድ የመታትን ኳስ የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ እንዴትም ብሎ አድኖበታል። ከዚህ ሙከራ ውጪ ሌላ አደገኛ የሚባል እምብዛም የግብ ሙከራ ሳያስመለክቱ ጨዋታው ያለግብ ሊጠናቀቅ ተገዷል።

ከሱ በማስከተል 5:00 ላይ ስልጤ ወራቤን ከአዲስ አበባ ከተማ ያገናኘው መርሐግብር ከዕረፍት በፊት እና ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩ ግቦች በአዲስ አበባ ከተማ የበላይነት ተጠናቋል። ጨዋታው እንደተጀመረ የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት አዲስ አበባዎች ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ስልጤ ወራቤዎችም ግብ እስካተናገዱበት ደቂቃ ድረስ ጥሩ ፉክክር በማድረግ በመልሶ ማጥቃት አንዳንድ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። በግብ ሙከራ ብልጫ የወሰዱት አዲስ አበባዎች ግብ በማስቆጠር እንዲሁ ቀዳሚ ነበሩ። በ32ኛው ደቂቃ ሄኖክ ካሳሁን ከመሃል ሜዳ የሰነጠቀለት ኳስ ኤርሚያስ ኃይሉ ይዞ በመግባት ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ  በቀላሉ አስቆጥሮ አዲስ አበባ ከተማን መሪ አድርጓል። እንዲሁም በ40ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ግርማዬ አስፋው ከተከላካይ ጀርባ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ፍጥነት በመጠቀም ኳሷን በመድረስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ አታሎ በማለፍ ሁለተኛ ግብ በግሩም አጨራረስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪነታቸውን በማስፋት የመጀመሪያውን አጋማሽ ጨርሰው ወደ መልበሻ ክፍል ገበተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ስልጤ ወራቤ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጠንከር ብሎ ገብቷል። በዚህም ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ወደ ጨዋታው መመለስ የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። በ49ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ስዩም ደስታ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ስልጤዎች ወደ ጨዋታ እንዲመለሱ አስችሏቸዋል። በተደጋጋሚም የግብ ማግባት ሙከራ ስልጤ ወራቤዎች ያደረጉ ሲሆን አቻ መሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ በ80ኛው ደቂቃ ወራቤዎች የቆመ ኳስ አግኝተው ኪዳነማሪያም ተስፋዬ መቷት የግብ አግዳሚ መልሶባቸዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው ላይ የስልጤ ወራቤው ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች ኳሷን ለማራቅ ሲሉ በፈጠሩት አለመግባባት ስህተቱን በመጠቀም ተቀይሮ የገባው ቢኒያም ታከለ በ90+6′ ላይ ሶስተኛውን ግብ ለአዲስአበባ ከተማ አስቆጥሮ ጨዋታው በአዲስአበባ ከተማ ሶስት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሦስተኛው ጨዋታ ስምንት ሰዓት ላይ ጅማ አባ ጅፋርን ከይርጋጨፌ ቡና አገናኝቶ በፊልሞን ገ/ፃዲቅ ብቸኛ ግብ ጅማ አባጅፋርን አሸናፊ በማድረግ ተጠናቋል። ብዙ የግብ ሙከራ ያላስመለከተው ሦስተኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ይርጋጨፌ ቡና ጥሩ የኳስ ቅብብል እና ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎች መፍጠር የቻለ ቡድን ነበር። ሆኖም ግን አስቆጪ የሚባል አደገኛ ሙከራ ሲያደርጉ አልተስተዋሉም። ጅማ አባ ጅፋሮችም ብዙም የኳስ ቅብብል ባያደርጉም በጥንቃቄ ግብ እንዳይቆጠርባቸው በመከላከል ረገድ ጥሩ የሆኑበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል። የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት በ44ኛው ደቂቃ ይርጋጨፌ ቡናዎች ኳስ ይዘው ሲገቡ የጅማ አባጅፋር ተጫዋች የሆነው ማንያዘዋል ካሣ ባደረገው እጅ ንክኪ ፍፁም ቅጣት ምት ለይርጋጨፌ ቡና ተሰጥቷቸዋል። ምናልባትም እየመሩ ዕረፍት መውጣት ሚችሉበትን አጋጣሚ ቢሆንም ፍፁም ቅጣት ምቱን መልአልኤል ብርሃኑ አምክኗት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባጅፋር ጠንከር ብለው ሲመለሱ ግብ ለማስቆጠር ጫና ሲፈጥሩ ተስተውለዋል። በዚህም ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። በ51ኛው ደቂቃ ላይ ጅማ አባ ጅፋሮች በነቢል አብዱሰላም አማካኝነት ኳስን ይዘው ሲገቡ የይርጋጨፌ ቡናው ተከላካይ ጌታያውቃል ሮማን በነቢል ላይ በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አባጅፋሮች አግኝተው ፊልሞን ገ/ፃዲቅ ወደግብነት ቀይሮታል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደኋላ ያፈገፈጉት ጅማ አባጅፋሮች ነጥቡን ለማስጠበቅ በሚገባ ተከላክለዋል። ይርጋጨፌ ቡና በአንፃሩ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተረጋግተው ኳስን ተቆጣጥረው የተጫወቱ ቢሆንም በተለይም ግብ ካስቆጠረ በኋላ ጠንከር ብሎ የተመለሰውን የጅማ አባጅፋርን ተከላካይ መስመር አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው ተገባዷል።


በሳምንቱ ማሳረጊያ ጨዋታ ወልዲያ ከኦሮሚያ ፖሊስ ተገናኝተው ኦሮሚያ ፖሊስ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠሩት ግብ ሶስት ነጥብ አሳክተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ጥሩ የነበሩት ወልዲያዎች ከተደጋጋሚ ግብ ሙከራ በኋላ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ኦሮሚያ ፖሊስም ጥሩ የኳስ ቅብብል ቢያደርግም ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል። በ22ኛው ደቂቃ በድሩ ኑሩሁሴን ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ በማስቆጠር ወልዲያን መሪ አድርጓል። ኦሮሚያ ፖሊስ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ወልዲያዎችም ግብ ላለማስተናገድ ወደኋላ ተስበው በመጫወት  አልፈው አልፈው በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥሩ በመንቀሳቀሳቸው የመጀመሪያው አጋማሽ በወልዲያ መሪነት ለመጠናቀቅ ተገዷል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ጠንከር ብሎ የገባው ኦሮሚያ ፖሊስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ከዕረፍት መልስ አምስት ደቂቃ ነበር የጠበቁት። በ50ኛው ደቂቃ ኃይሌ ዘመድኩን ያሻገረለትን ኳስ ዳንኤል ዳርጌ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ጨዋታው ፉክክሩ እንዲደራ አድርጓል። ግብ አስቆጥረው ወደጨዋታ የተመለሱት ኦሮሚያ ፖሊሶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የግብ ሙከራ አድርገዋል። አደገኛ ሙከራ የሚባለውን በ59ኛው ደቂቃ ኃይሌ ዘመድኩን ርቀት ላይ የመታት ኳስ ለትንሽ ከፍ ብላበታለች። ሁለቱም ቡድኖች የማሸነፊያ ግብ ለማስቆጠር ቶሎ ቶሎ ወደተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል መግባት ችለዋል። ሙሉ የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት ኦሮሚያ ፖሊሶች በተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ሳያስቆጠሩ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ ሲታይ የመጨረሻ ዕድል የሆነችውን አጋጣሚ ከቆመ ኳስ አግኝተው ተቀይሮ የገባው አብዱከሪ አሊ ወደግብ ሲመታት ፋሲል አማረ በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ኦሮሚያ ፖሊስን አሸናፊ አድርጓል።