ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አርባምንጭ ከተማ መሪነቱን አጠናክሯል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 19ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐግብር ዛሬ አራት ጨዋታዎች ተደርገው አርባምንጭ ከተማ፣ ወሎ ኮምቦልቻ እና አዲስ ከተማ ድል አስመዝግበዋል።


በዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ የካ ክ/ከተማ ከቦዲቲ ተገናኝተው ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል። ጥሩ ፉክክር በተስተናገደበት ጨዋታ ቦዲቲዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ኤፍሬም አበራ ከውብሸት ወልዴ ጋር ተቀባብሎ ያገኛትን ኳስ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያወጣበት የሚጠቀስ ሙከራ ነበር። በየካ በኩልም አንተነህ እና ጁንዴክስን ማዕከል ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የጎል እድል ለመፍጠር ቢሞክሩም ጎል ሳንመለከት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የካዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን ቦዲቲዎች ደግሞ የተሻለ የመከላከል አደረጃጀት ያሳዩበት አጋማሽ ነበር። በ61ኛው ደቂቃ በየካ በኩል ጁንዴክስ አወቀ ያገኘውን መልካም አጋጣሚ ወደ ግብ ሞክሮ ተከላካዮች በግሩም ሁኔታ ተደርበው ያወጡበት የሚጠቀስ ሙከራ ሲሆን ቦዲቲዎች በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች የበላይነት በመውሰድ ቢጫወቱም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታቸው 0ለ0 ተጠናቋል።

በመቀጠል በተደረገው ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻ ደብረብርሃን ከተማን 1-0 በማሸነፍ ወሳኝ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል።

በመጀመርያው አጋማሽ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው መጫወት የቻሉት ደብረብርሃኖች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ቢሆኑም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው የታዩ ሲሆን በአብዱልመጂድ ሁሴን አማካኝነት ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው ያዳነበት የሚጠቀስ ሙከራ ነበር። በመልሶ ማጥቃት እና ለአጥቂዎች በሚጣሉ ኳሶች ወደ ግብ ለመቅረብ ጥረት ያደረጉት ኮምቦልቻዎችም በተመሳሳይ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ የመጀመርያው አጋማሽ ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ በተመሳሳይ ሁኔታ ጨዋታው ቀጥሎ ደብረብርሃኖች ለማጥቃት ወደ ኮምቦልቻ በተጠጉበት ወቅት ያቋረጡትን ኳስ ወደ ደብረብርሃን የግብ ክልል በመልሶ ማጥቃት ሲያመሩ በተሠራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ኢምራን ሱለይማን አስቆጥሮ በ67ኛው ደቂቃ ኮምቦልቻን ቀዳሚ አድርጓል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ደብረብርሃኖች ተጭነው በመጫወት የአቻነት ጎል ፍለጋ ቢንቀሳቀሱም በተደጋጋሚ ያደረጓቸውን ሙከራዎች በጨዋታው ኮከብ ግብ ጠባቂው ታሪኩ አረዳ ጥረት ጎል ሳይሆኑ ቀርተዋል። ጨዋታውም በወሎ ኮምቦልቻ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በሦስተኛው የዕለቱ መርሐግብር አርባምንጭ ከተማ ቢሾፍቱ ከተማን ገጥሞ 2-0 በማሸነፍ የምድቡን መሪነት ማስፋት ችሏል።

ጨዋታው እንደጀመረ ወደ ቢሾፍቱ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በማምራት መፈተሽ የጀመሩት አርባምንጮች ጎል ለማስቆጠር ብዙም ደቂቃ አልፈጀባቸውም። አራተኛው ደቂቃ ላይ እንዳልካቸው መስፍን በራሱ ጥረት ገፍቶ በመሄድ ከሳጥን ውጪ መትቶ አርባምንጭን ቀዳሚ ያደረገ ሲሆን ራሱ እንዳልካቸው በድጋሚ በ12ኛው ደቂቃ ከአህመድ ሁሴን ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወደ ውስጥ በመግባት አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሊያወጣበት ችሏል።

ቢሾፍቱዎች ቀስ በቀስ ራሳቸውን በማረጋጋት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የአርባምንጮችን የኋላ ክፍል መፈተን ያልቻሉ ሲሆን በአርባምንጭ በኩል በአጋማሹ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጣሪው እንዳልካቸው ኳስ በእጁ በመንካቱ የማስጠንቀቂያ ካርድ ሲመለከት ከዳኛ ጋር እሰጥ እገባ በመግባቱ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ወጥቶ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አርባ አምስት ቢሾፍቱዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻለ የበላይነት ቢኖራቸውም የጎል ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩ ሲሆን ውጤታቸውን ለማስጠበቅ የተንቀሳቀሱት አርባምንጮች በጭማሪ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው ፍቃዱ መኮንን ተጨማሪ ጎል አግኝተው ጨዋታው 2-0 ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በሊጉ ሽንፈት ያልገጠማቸው አርባምንጮች ከተከታዩ ነገሌ አርሲ ያላቸውን ልዩነት ወደ 11 ከፍ በማድረግ ወደ ፕሪምየር ሊግ የመመለስ ግስጋሴያቸውን አሳምረዋል።


በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ግርጌ ላይ ሆኖ ጨዋታውን ያደረገው አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ነገሌ አርሲን 2-1 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል።

በመጀመርያው አጋማሽ ነገሌ አርሲዎች የተሻለ የበላይነት ይዘው ቢንቀሳቀሱም የጎል ዕድል በመፍጠር የተሻሉ የነበሩት አዲስ ከተማዎች መሪ መሆን ችለዋል። በ14ኛው ደቂቃም በረከት ብርሃኑ ላይ በተሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ቅዱስ ተስፋዬ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪ መሆን ችለዋል።

ከጎሉ በኋላ የአቻነት ጎል ፍለጋ የተንቀሳቀሱት አርሲዎች በ30ኛው ደቂቃ ገብረመስቀል ዱባለ ላይ በተሠራ ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ቢችሉም ራሱ ገብረመስቀል መትቶ ግብ ጠባቂው ሊያመክንበት ችሏል። ከ9 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቶስላች ሳይመን ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ አቻ አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመርያው ተመሳሳይ ሂደት የነበረው ሲሆን 53ኛው ደቂቃ ላይ በቅዱስ ተስፋዬ ላይ የተሠራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በረከት ብርሃኑ በአግባቡ ተጠቅሞ አዲስ ከተማን በድጋሚ መሪ አድርጓል።

ከአዲስ ከተማ መሪነት በኋላ አርሲ ነገሌዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢያደርጉም ጥሩ የመከላከል እንቅስቃሴ ያሳዩት አዲስ ከተማዎች መረባቸውን ሳያስደፍሩ ጨዋታውን 2-1 አሸንፈው ወጥተዋል።

ድሉ ለአዲስ ከተማ ክ/ከተማ በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ድል ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌም ለካፋ ቡና አስረክበዋል።