ሪፖርት | እጅግ ማራኪው ጨዋታ በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተቋጭቷል

የሳምንቱ ማሳረጊያ በነበረው እና ለዕይታ ሳቢነቱ ሳይደበዝዝ ፍፃሜውን ባገኘው ጨዋታ አዳማ ከተማ በዮሴፍ ታረቀኝ ብቸኛ ጎል ኢትዮጵያ ቡናን 1ለ0 በመርታት ከሽንፈት ወደ ድል ተመልሰዋል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በሽርፍራፊ ሰከንድ ጎል ከሀዋሳ ላይ ሙሉ ነጥብን የወሰደውን ቡድን ሳይለውጡ ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት አስተናግደው በነበሩት አዳማ ከተማዎች በኩል ግን በተደረጉ ሦስት ቅያሪዎች ቅጣት ባስተናገደው ታዬ ጋሻው ፣ ነቢል ኑሪ እና ሳዲቅ ዳሪ ቦታ ሱራፌል ዐወል ፣ አቡበከር ሻሚል እና ከቅጣት የተመለሰው ቢኒያም አይተን ተክተዋቸው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ረጅም ጊዜያትን በህክምና አሳልፎ በትላንትናው ዕለት ህይወቱ ላለፈው የቀድሞው የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ እና የወጣት ቡድኑ የአሰልጣኝ ቡድን አባል ለነበረው ሱራፌል ስዩም የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኋላ በመሐል ዳኛው ቢኒያም ወርቅአገኘሁ አጋፋሪነት ጨዋታው ተጀምሯል። ለዕይታ ማራኪ መልክን ተላብሶ በጀመረው ጨዋታ ተመሳሳይ ቅርፅን ቡድኖቹ ተከትለው በሽግግር አጨዋወት ንክኪዎችን አብዝቶ በመጠቀም ከሳጥን ሳጥን በአንድ ሁለት አልያም ወደ መስመር ባዘነበለ እንቅስቃሴ ሁለቱም ተጋጣሚዎች  ሲጫወቱ ያስተዋልን ሲሆን የግብ አጋጣሚዎችን መመልከት የቻልነው ግን ጨዋታው ሀያዎቹን ደቂቃዎች ሲሻገር ነበር።

የተጋጣሚን እንቅስቃሴ ጫና ውስጥ በመክተት መሐል ሜዳው ላይ በሚደረጉ ቅብብሎች ወደ ቀኝ መስመር በማጋደል ለመጫወት የሞከሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከቀኝ ወደ ውስጥ ከተከላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ አንነተህ ተፈራ በግንባር ገጭቶ ሰይድ ሀብታሙ በጥሩ ብቃት  ኳሷን ያመከነበት አጋጣሚ የጨዋታው ቀዳሚ ሙከራ ሆናለች። ከተደረገባቸው ሙከራ መልስ በተረጋጋ ሽግግር መልሶ ማጥቃትን የተጠቀሙት አዳማ ከተማዎች 25ኛው ደቂቃ ቢኒያም ዐይተን ወደ ግራ ላዘነበለው ዮሴፍ ታረቀኝ በዐየር የሰጠውን ኳስ ከበረከት አማረ ጋር ተጫዋቹ ቢገናኝም የግብ ዘቡ መልካሟን አጋጣሚ ከጎልነት አግዶበታል።

ከፍ ያሉ ተነሳሽነቶችን እያስመለከተን ቀጣዮቹን ደቂቃዎች ያስጓዘን ጨዋታው 29ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ አዳማ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ቡናማዎቹ ባመሩበት ወቅት በሳጥን ውስጥ አማኑኤል አድማሱ ላይ ሱራፌል ዐወል ከጀርባው ሆኖ መጥለፉን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት መስፍን ታፈሠ ቢመታውም የግቡ አግዳሚ ብረትን ኳሷ ለትማ የወጣችበት ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን በመልሶ ማጥቃት ወደ ቡናማዎቹ የግብ ክልል ፈጥነው ያመሩት አዳማ ከተማዎች ጀሚል ከቀኝ ወደ ጎል መቶ በረከት አማረ የተፋትን ኳስ ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ጎልነት ቀይሯት ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከጎሏ በኋላ መነቃቃትን እያሳዩ አቻ ሊሆኑ የሚችሉባቸውን ዕድሎችን ለመፍጠር የሚታትሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ተቆጣጥረው የተጋጣሚ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ቢደርሱም የሰይድ ሀብታሙን መረብ ለመድፈር በሚታይባቸው መቻኮሎች የተነሳ ሳይሳካላቸው ጨዋታው በአዳማ ከተማ 1ለ0 መሪነት ተገባዷል።

ከዕረፍት በተመለሰው ጨዋታ ማራኪነቱን ሳይቀንስ በፉክክሮች የቀጠለ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናዎች ሙሉ በሙሉ በፕረሲንግ ጫናን በማሳደር ወደ ጨዋታ ለመመለስ ብርቱ ትግልን ከአጋማሹ መጀመር አንስቶ ያስመለከቱን ሲሆን አዳማ ከተማዎች ጥንቃቄ ላይ ባዘነበለ መጠነኛ መልሶ ማጥቃት የተጫወቱበትን ሒደት አስተውለናል። አብዱልከሪም ወርቁ በነገሰባቸው እና ሰይድ ሀብታሙ በደመቀበት የጨዋታው የመጨረሻዎቹ ሀያ ያህል ደቂቃዎች ፈጣን አጀማመርን አድርገው የነበሩት ቡናማዎቹ ከአብዱልከሪም ወርቁ በሚነሱ ያለቀላቸው መነሻ ኳሶች አጋጣሚዎችን አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። 50ኛው ደቂቃ ከመሐል ክፍል አብዱልከሪም የሰነጠቀለትን ኳስ አማኑኤል አድማሱ ከግቡ ትይዩ ሆኖ ያገኛትን አጋጣሚ የግብ ዘቡ ሰይድ ሀብታሙ መክቶበታል። 54ኛው ደቂቃም ላይ በድጋሚ ከማዕዘን አብዱልከሪም ያሻማውን ወልደአማኑኤል ጌቱ በግንባር ገጭቶ በጨዋታው የጎመራው ግብ ጠባቂው ሰይድ ኳሷን አፅድቶበታል።

አብዱልከሪም ከሚሰጣቸው ኳሷች በተጨማሪ እየነዳ ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት በግሉ አቅሙም ዕድሎችን መፍጠር ቢችልም የሰይድ መረብ መድፈር ላይ ግን በእጅጉ ተቸግሮ ተስተውሏል። ረጅሙን ደቂቃ ወደ መከላከሉ አዘንብለው ጥንቃቄን የመረጡት አዳማዎች በመልሶ ማጥቃት በቢኒያም የሚያስቆጭ ዕድልን ፈጥረው ወጣቱ አጥቂ ከተዘናጋበት እና 63ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሱራፌል ዐወል አክርሮ መቶ የግቡ ብረት ለትማ ኳሷ ወጥታለች። ፈጣን በሆኑ አንድ ሁለት ንክኪዎች ብልጫን በመውሰድ ቶሎ ቶሎ የአዳማ ተከላካዮች ጋር የሚደርሱት የቡና አጥቂዎች በድግግሞሽ ዕድሎችን ቢፈጥሩም የስልነት ድክመቶች በጉልህ ተንፀባርቆባቸዋል።

67ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም በረጅሙ ወደ ግቡ አሻግሮ የሰጠውን አንነተህ ነፃ ሆኖ አግኝቶ ያመከናት ሲሆን 73ኛው ደቂቃ ላይም ከቀኝ የተሻማን ኳስ መስፍን በግንባር ገጭቶ የሰይድ የነቃ የግብ አጠባበቅ ከጎልነት አትርፏታል። የሚያገኙትን ግልፅ ዕድሎች አለማስቆጠራቸውን ተከትሎ በመልሶ ማጥቃት ይጋለጡ የነበሩት ቡናማዎች 76ኛው ደቂቃ ቢኒያም ዐይተን ግልፅ የማስቆጠር አጋጣሚን አግኝቶ በረከት አማረ ከግብ ክልሉ ለቆ ወጥቶ ኳሷን አስጥሎታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጡ አምስት ጭማሪ ደቂቃዎች ውስጥ 90+1 ላይ ዮሴፍ የአዳማን የግብ መጠን ከፍ የምታደርግ ያለቀላትን ኳስ አግኝቶ ወደ ጎል ሞክሮ የግቡ ቋሚ ብረት ከመለሳት በኋላ እጅግ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ማራኪው ጨዋታ በአዳማ ከተማ 1ለ0 ድል አድራጊነት ተፈፅሟል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ ጨዋታው ለተመልካች አዝናኝ እንደነበር ጠቁመው ተጫዋቾቹ የሚችሉትን ቢያደርጉም በአላስፈላጊ ጉጉት በርካታ የግብ ዕድሎችን ማምከናቸውን በመግለጽ ከእንቅስቃሴያቸው አንጻር ውጤቱ በቂ እንዳልሆነ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ከሌላ ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ እንዳደረጉ ተናግረው የተሳተላቸው የፍጹም ቅጣት ምት ውጤት ቀያሪ እንደነበር በመጠቆም በቅርብ ሳምንታት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፋቸው ለአሰልጣኝነት ሕይወታቸው ወሳኝ እንደሆነ ገልጸው ለዋንጫውም ተስፋ እንዳላቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።