ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ደሴ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ተከታታይ ድል አስመዝግበዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ 20ኛ ሳምንት የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች ተደርገው ደሴ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ አሸናፊ ሆነዋል።

በዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደሴ ከተማ ተከታዩ ሸገር ከተማን ገጥሞ 4-2 አሸንፏል።

በጨዋታው ጅማሮ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉት ሸገሮች በግብ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ሸገሮች በጥሩ ቅብብል ወደፊት ይዘው ሂደው ሳጥን ውስጥ ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አንዋር አብዱልጀባር በግሩም ሁኔታ ወደ ጎልነት ቀይሮ መሪ መሆን ችለዋል።

ከጎሉ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተንቀሳቀሱት ደሴዎች በ24ኛው ደቂቃ አቻ የሚሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። ከግራ መስመር አንሷር በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ሙሉጌታ ከተከላካዮች ጋር ኳስ ለማግኘት ሲታገል የተመለሰውን ኳስ ብሩክ ቦጋለ ከሳጥን ውስጥ በቅጥታ መትቶ ወደግብነት ቀይሯል።

በግቡ የተነቃቡቁት ደሴዎች የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ቀጥለው 39ኛው ደቂቃ ላይ አቡሽ ደርቤ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ኢብራሂም ከድር አስቆጥሯል። ጎሉ ሲቋዮጠር ግብ ጠባቂው ላይ ጥፋት ተሰርቷል በሚልም ሸገር ከተማዎች ቅሬታ ያሰሙ ሲሆን የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ የሸገር ከተማ ቡድን መሪ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ደሴዎች መሪነታቸውን ያሰፉበትን ጎል በቶሎ አግኝተዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ ወደ ሸገር የግብ ክልል የተጣለውን ኳስ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ ከጎሉ ወጥቶ ለማውጣት ቢሞክርም ኳሱ አምልጦት አቡሽ ደርቤ በአግባቡ በመጠቀም ወደ ጎልነት ቀይሯል።

55ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል አስማማው ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ሸገሮች የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን አጥቂው ፋሲል አስማማው አስቆጥሮ ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። ደሴዎች የፍፁም ቅጣት ምቱ የተሰጠበት ውሳኔ አግባብ አይደለም በሚል ቅሬታ ያነሱ ሲሆን በውዝግቡም የቡድን መሪው በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

በውዝግቦች የተሞላው ጨዋታ ቀጥሎ የመደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂ በቀጥታ የተሻገረውን ኳስ ሙሉጌታ ካሳሁን ከተከላካዮች ታግሎ በመቆጣጠር አመቻችቶለት ፀጋ ደርቤ በማስቆጠር ጨዋታው በደሴ ከተማ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው ጨዋታ በኮምቦልቻ እና ባቱ መካከል ተደርጎ ኮምቦልቻዎች 2-0 አሸንፈዋል።

ወሎ ኮምቦልቻዎች ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ ጎል ለማስቆጠር ብዙም ጊዜ አልፈጀባቸውም። በጥሩ መልሶ ማጥቃት ይዘው የሄዱትን ኳስ ማኑሄ ጌታቸው ተቆጣጥሮ በ8ኛው ደቂቃ በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል።

ከጎሉ በኋላ ባቱዎች ኳሱን በመቆጣጠር የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው መጫወት ችለዋል። በተለይም በ18ኛው ደቂቃ የሺጥላ ዳቢ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያወጣበት እና 24ኛው ደቂቃ ላይ ዮሐንስ ደረጄ ወደ መትቶ ኳሱ ግብ ጠባቂውን ቢያልፍም ተከላካይ ያወጣበት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።

ከእረፍት መልስም ባቱዎች ኳሱን በመያዝ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም በጥንቃቄ በመጫወት ውጤታቸውን ለማስጠበቅ የተጫወቱት ወሎ ኮምቦልቻዎች አጨዋታወታቸው ፍሬ አፍርቶ 87ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ቢላል ገመዳ ከማኑሄ ጌታቸው ጋር ጥሩ ቅብብል አድርገው ወደ ውስጥ በመግባት ቢላል መሪነታቸውን ያሰፉበት ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በወሎ ኮምቦልቻ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ተከታታይ ሦስተኛ ድሉን ያስመዘገበው ወሎ ኮምቦልቻ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚያርገውን ጥረት ቀጥሎ ደረጃውን በጊዜያዊነት 10ኛ ላይ አስቀምጧል።