ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ኤሌክትሪክ እና ንብ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 20 ሳምንት ዛሬ በሁለተኛ ቀን በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነቱን ሲያጠናክር ንብ ወደ ድል ተመልሷል።

ረፋድ ሦስት ሰዓት የተደረገው መርሃግብር ጅማ አባጅፋርን ከቤንች ማጅ ቡና አገናኝቶ ከእረፍት በፊትና ከእረፍት መልስ በተቆጠሩ ግቦች ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

ጅማ አባጅፋር ፍፁም የጨዋታ በላይነት እና የግብ ማግባት እድል የፈጠሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሲያሳልፍ ቤንች ማጂ ቡና ኳስ ቀጥጥር ላይ ጥሩ ቢሆኑም በማጥቃት ረገድ ደካማ የሆኑበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ለማሳለፍ ተገደዋል። ይህንን ክፍተት በሚገባ የተጠቀመው ጅማ አባጅፋር የሚያገኙትን ኳሶች ወደግብነት ለመቀየር ሙከራ ሲያደርጉ ታይተዋል። ገና ከ6ኛው ደቂቃ ጀምረውም ግብ ማስቆጠር ጀምረዋል። በ6ኛው ደቂቃ አሚር አበዳ በቤንች ማጅ ቡና ተከላካዮች መካከል የሰነጠቀለትን ኳስ ፈልሞን ገብረፃዲቅ አግኝቶ በቀላሉ አስቆጥሮ ጅማ አባቡናን ቀዳሚ አድርጓል።

ጅፋሮች የቤንች ማጅ ቡናን ድክመት በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ያስቆጠሩ ሲሆን እረፍት ሊወጡ ሰከንዶች ሲቀራቸው አዩብ አዳሙ ከመሰመር የተሻማውን ኳስ አየር ላይ እንዳለች በጥሩ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፏል። ተጨማሪ ደቂቃ ላይም ጅማ አባጅፋሮች ምናልባትም ሶስት ለምንም እየመሩ ወደመልበሻ ክፍል መግባት የሚችሉበትን አደገኛ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን አሚር አበዳ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለ ኳስ አግንቶ ግብ ጠባቂው መውጣቱን ተከትሎ በቀላሉ ከፍ በማድረግ የመታት ኳስ የግብ ቋሚ ብረት መልሶበት ወደ እረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ክብደቱን ጨምሮ ቤንች ማጂ ቡናን ጠንክሮ ሲመለስ ጅማ አባጅፋር ደግሞ ነጥቡን ለማስጠበቅ የመከላከል ባህርይ ያሳዩበት ሆኖ ቀጥሏል። በ51ኛው ደቂቃ ሙሉቀን ተሾመ በግሩም አጨራረስ ግብ በማስቆጠር ጨዋታው 2ለ1 እንዲሆን አድርጎ ቤንች ማጅ ቡናን ወደ ጨዋታ እንዲመለስ አድርጓል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ቤንች ማጅ ቡናዎች በመነቃቃት ወደ ጨዋታ የተመለሱ ሲሆን የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሰባት ደቂቃ ብቻ ጠብቀዋል። በአንድ ለአንድ ንክኪ ወደ ግብ ክልል ሲጠጉ የጅማ አባጅፋሮች ግብ ጠባቂ ኳሷን ለማዳን ወደ ውጪ መውጣቱን አይቶ ሙሉቀን ተሾመ በቀላሉ ኳሷን ከፍ በማድረግ መረብ ላይ አሳርፎ ጨዋታው 2ለ2 እንዲሆን ሆኗል።

አቻ ከሆኑ በኋላም የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት ቤንች ማጅ ቡናዎች የማሸነፊያ ግብ ለማስቆጠር፣ ጅማ አባጅፋሮችም አልፈው አልፈው በሚያደርጉት ሙከራ ጨዋታው ቀጥሎ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለተኛው ጨዋታ ጅማ አባቡናን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቶ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-0 በማሸነፍ መሪነቱን ማጠናከር የቻለበትን ሶስት ነጥብ አሳክቷል።

ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ለማሰቆጠር ኳስ አደራጅተው ያገኙትን አጋጣሚ ወደግብ ለመቀየር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በዚህም ግቦች አከታትለው ማስቆጠር ችለዋል። በ11ኛው ደቂቃ በቅብብል የተገኘውን ኳስ አቤል ሀብታሙ አግኝቶ ኢትዮ ኤሌክትሪክን መሪ አድርጓል። በድጋሚ ሌላ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በቶሎ ወደ ግብ የገቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ13ኛው ደቂቃ መሳይ ሰለሞን የመታት ኳስ የግብ ቋም ብረት መልሶበታል።

በ14ኛው ደቂቃ ልዑልሰገድ አስፋው ቢኒያም ካሳሁን ያሻገረለት ኳስ ከመስመር በኩል ሆኖ በግሩም አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የግብ ልዩነት እንዲያሰፋ ሆኗል። እንዲሁም በ25ኛው ደቂቃ አደገኛ የማጥቃት ሙከራ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በብሩክ ዩሐንስ አማካኝነት ያደረጉ ሲሆን ጥላሁን ቦቼ ያሻማትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርግም የግብ ቋም ብረት መልሶበታል። ጅማ አባ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረገበት ሆኖ ወደ እረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም ጠንከር ብለው የገቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከባባድ ሙከራዎችን በማድረግ ጫና ሲያደርጉ በ52ኛው ደቂቃ ያሬድ የማነ በመሰመር በኩል አክርሮ በመምታት ያደረጉትን ሙከራ የጅማ አባቡናው ግብ ጠባቂ እንደምንም አድኖታል። ጅማ አባ ቡና በአንፃሩ ከመጀመሪያው አጋማሽ ሲነፃፃር ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን ግብ ለማስቆጠርም በአንድ ለአንድ ቅብብል ወደተጋጣሚ ቡድን ግብ ክልል መግባት የቻሉ ቢሆንም የኤሌክትሪክን ተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ደቂቃዎች ገፍተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጨማሪ ግብ መሆን ሚችሉበትን አጋጣሚዎች መድረሻቸውን አቤል ሀብታሙ ላይ ባደረጉ ኳሶች በተደጋጋሚ አድርገዋል። ሆኖም ግን ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት ለምንም በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተገባዷል።

ሦስተኛው ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማን ከንብ አገናኝቶ ንብ 2-0 አሸንፏል።

ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባስመለከተው በ10:00 ጨዋታ ንብ በኳስ ቁጥጥር እና በሙከራዎች ጥሩ በመሆን ግብ ለማስቆጠር ቶሎ ቶሎ ወደተቀራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲገቡ ተስተውለዋል።  የጥረታቸው ውጤት የሆነችዋን ኳስ በ7ኛው ደቂቃ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በአንድ ለአንድ ቅብብል ወደ አዲስ አበባ ከተማ ግብ ክልል የገቡት ምስክር መለሰ እና ኢዮብ ደረሱ የተሳካ ቅብብል አድርገው ምስክር መለሰ ኳስን ከመረብ ጋር አገናኝቶ ንብን መሪ አድርጓል።

የአቻነት ግብ ለማስቆጠር አዲስ አበባ ከተማ ኳስ መስርቶ በመጫወት መደረሻቸውን ኤርሚያስ ኃይሉ ያደረጉ ኳሶች ወደፊት ቢደረሱትም ለማስቆጠር ሲቸገር ተስተውሏል። በ44ኛው ደቂቃ ላይ በቆመ ኳስ ያገኙትን አጋጣሚ ረመዳን ናስር ቀጥታ ወደግብ ሲመታት ኳሷን የግብ ቋም ብረት መልሶባቸው 1ለ0 እየተመሩ ወደመልበሻ ክፍል ለመግባት ተገደዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ንብ ጥንካሬ ጨምረው ኳስ ይዘው ወደፊት ሲገቡ ተስተውለዋል። በ49ኛው ደቂቃ ታምራት ስላስ በራሱ ጥረት ኳስ እየገፋ ይዞ ገብቶ ግሩም ኳስ መረብ ላይ አሳርፎ ንብ 2ለ0 እንዲመራ አድርጓል። አዲስ አበባ ከተማ በኳስ ቁጥጥር ብሎም ግበ ለማስቆጠር በሚያደርጉት ሙከራ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ኳስና መረብ አስታርቆ ግብ ለማስቆጠር ተችገረዋል። በርከት ያለ ኳስ ይዘው ቢገቡም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክት በንብ አሸናፊነት ተጠናቋል።