ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ጋሞ ጨንቻ እና ቢሾፍቱ ከተማ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የ20ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ጋሞ ጨንቻ እና ቢሾፍቱ ከተማ ድል ሲቀናቸው ኦሜድላ እና ቦዲቲ ነጥብ ተጋርተዋል።

በዛሬ የመጀመርያ መርሐ ግብር ኦሜድላ ከ ቦዲቲ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል። ጨዋታው በጥቅሉ ጥሩ እንቅስቅሴ የታየበት ቢሆንም እምብዛም የጎል እድል የተፈጠረበት ሳይሆን ቀርቷል።

በመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት ቦዲቲዎች በ13ኛው ደቂቃ በውብሸት ወልዴ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ሞክሮ የጎሉ ብረት ገጭቶበት የወጣበት የሚጠቀስ ሲሆን በረጃጅም ኳሶች የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት ኦሜድላዎች በኩል ቻላቸው ቤዛ ያደረገው ሙከራ የሚጠቀስ ነው።

ከእረፍት መልስ ኦሜድላዎች የተሻለ ብልጫ አሳይተው የተንቀሳቀሱ ሲሆን 75ኛው ደቂቃ ላይ ከተመስገን የተሻገረለትን ኳስ ጌታቸው አርትሮ በደረቱ አውርዶ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ካወጣበት ተጠቃሽ ሙከራ በቀር በሁለቱም በኩል እምብዛም ሙከራዎች ሳንመለከት ያለ ጎል ተጠናቋል።

ቀጥሎ በተደረገው ጨዋታ ደብረብርሀን ከተማን የገጠመው ጋሞ ጨንቻ 2-1 አሸንፏል። ሁሉም ጎሎች በተቆጠሩበት የመጀመርያ አጋማሽ በደጋፊዎች ታጅበው በጥሩ መነሳሳት የተጫወቱት ጋሞ ጨንቻዎች በጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። 19ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ፊት በመሄድ ማቲያስ ከመስመር ወደ ውስጥ በመግባት መትቶ በረኛው ሲመለስበት ፋሲካ አለኝታ አግኝቶ በማስቆጠር መሪ ሆነዋል።

ኳስ በመቆጣጠር የተሻሉ የነበሩት ደብረብርሀኖች የአቻነት ጎል ፍለጋ ባደረጉት እንቅስቃሴ አምበሉ ልደቱ ጌታቸው የመታውን ኳስ አቡሽ አበበ የመለሰበት የሚጠቀስ ሙከራ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የተንቀሳቀሱት ጋሞዎች በ31ኛው ደቂቃ በያሬድ መኮንን አማካኝነት መሪነታቸውን አስፍተዋል።

ደብረብርሀኖች የመጀመርያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ልዩነቱን አጥብበዋል። ሙሉቀን ተስፋዬ ከአብዱልከሪም መሐመድ የተመቻቸለትን ኳስ  አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታው በመመለስ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ደብረብርሀኖች አቻ ለመሆን ጥረት ያደረጉ ሲሆን ተጭነው በመጫወት ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረገው የጋሞ ጨንቻው ግብ ጠባቂ አቡሽ አበበ ጥረት ጎል ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በጋሞ ጨንቻ 2-1 አሸናፊነት ፍፃሜ አግኝቷል።

በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ቢሾፍቱ ከተማ የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ካፋ ቡናን 2-1 በማሸነፍ ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

በጨዋታው ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ቢሾፍቱዎች በሙከራ ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን እንደተጀመረ አንድ ሁለት ተቀባብለው ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመሄድ ዳዊት ሽፈራው የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂ አውጥቶበታል። በካፋ ቡና በኩል ደግሞ 17ኛው ደቂቃ ላይ ያቤፅ ፍሬው ያደረገው ሙከራ የጎሉ ብረት ገጭተቶበት ወጥቷል።

ጨዋታው ቀጥሎ 41ኛው ደቁቃ ላይ አብዱላዚዝ ይዞ በመሄድ ለዳዊት ያመቻቸለትን ኳስ ዳዊት ከግብ ጠባቂ ተገናኝቶ አጨራረሱን በማሳመር ቢሾፍቱን ቀዳሚ አድርጎ ወደ እረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ካፋ ቡናዎች ጥሩ የማጥቃት አጀማመር ያደረጉ ሲሆን ከአስራ አምስት ደቂቃዎች በኋላ ያቤፅ በሳጥን ውስጥ በተሰራበት ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ዮናታን ከበደ በአግባቡ ተጠቅሞ ካፋ ቡናን አቻ አድርጓል።

ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ ቢሾፍቱዎች መልሰው መሪ የሚሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። 69ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል በኃይሉ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ለውጧል። ግብ ከተቆጠረ በኋላ ካፋዎች ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ በማድረግ አቻ ለመሆን ጥረት ቢያደርጉም ቢሾፍቱዎች የግብ ክልላቸውን ሳያስደፍሩ ጨዋታውም በቢሾፍቱ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።