መረጃዎች | 86ኛ የጨዋታ ቀን

22ኛ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀምራል። ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው ተሰናድተዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

በሰንጠረዡ ታችኛው ክፍል በሚደረገው ፉክክር ወሳኝነት ያለው የሳምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

አራት ሽንፈት አልባ ሳምንታት ያሳለፉት ወልቂጤ ከተማዎች የአስራ ሁለት ሳምንታት የወራጅ ቀጠና ቆይታቸው እንዲያበቃ የግድ ከዚ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ያስፈልጋቸዋል። ሠራተኞቹ ከአስከፊው የውጤት መጥፋት በኋላ አገግመው በጥሩ ጉዞ ይገኛሉ። መፍትሄ ካልተገኘለት የግብ ማስቆጠር ችግር በስተቀር ሁለንተናዊ የሚባል በጎ ለውጥ ያመጣው ቡድኑ በተለይም በመከላከሉ ረገድ ያመጣው ለውጥ እንደ ትልቅ ስኬት መውሰድ ግድ ይላል። የሠራተኞቹ የመከላከል አደረጃጀት በፈረሰኞቹ ሁለት ለባዶ ከተሸነፈ በኋላ ባከናወኗቸው አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ አላስተናገደም። ቡድኑ በመከላከል አደረጃጀቱ ካሳየው ጥንካሬ በተጨማሪ ጨዋታን ለመቆጣጠር ያሳየው ብርታትም የጥቃት መጠኑን እንዲቀንስ አስችሎታል ተብሎ ይታመናል።

ሆኖም የግብ ማስቆጠር ችግሩ የቡድኑ ትልቁ ክፍተት ተደርጎ ይወሰዳል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ማስተናገዱ እንደ ስኬት ቢቆጠርም በተጠቀሱት ጨዋታዎች ያስቆጠረው የግብ መጠን ግን አንድ ብቻ ነው። ቀጣይ ባሉት የሊጉ ቆይታ የሚወስኑለት ወሳኝ ጨዋታዎችም የግብ ማስቆጠር ችግር ፈትቶ መቅረብ ይኖርበታል።

ከአስራ ሁለት ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ከድል ጋር የታረቁት ኢትዮጵያ መድኖች ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ የቅርብ ተፎካካርያቸው ላይ ድል ማድረግ ይኖርባቸዋል። እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ላለፉት አራት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሱት መድኖች በሁለተኛው ዙር በብዙ ረገድ ተሻሽለዋል። ቡድኑ ከቆይታ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ አሸንፏል፤ ድሉም ከሊጉ መሪዎች አንዱ የሆነው ጠንካራው መቻል ላይ መሆኑ ደግሞ የቡድኑን መሻሻል ማሳያ ነው።

የፊት መስመሩ ጥንካሬ ሌላው በቡድኑ የታየ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ለውጥ ነው። ሽንፈት ባላስተናገደባቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ግቦች ያስቆጠረው ቡድኑ የቀደመ ድክመቱን በሚገባ አርሟል። ከተጠቀሱት መርሀ ግብሮች በፊት ባደረጋቸው አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ አስቆጥሮ የነበረው ቡድኑ የግብ ማስቆጠር አቅሙ በዚ መጠን ማሳደጉ ሌላው የቡድኑን ለውጥ ማሳያ ነው። የፊት መስመሩ ላለፉት አራት ጨዋታዎች ግብ ካላስተናገደው የተጋጣሚ የመከላከል አደረጃጀት የሚያደርገው ፍጥጫም የጨዋታውን ውጤት ሊወስኑ ከሚችሉ ኩነቶች አንዱ ነው።

ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ላለመውረድ በሚደረግ ፉክክር ውስጥ መኖራቸው እና ልዩነቱ የሦስት ነጥቦች ብቻ መሆኑ ጨዋታው ተጠባቂ ያደርገዋል። ከዛ በተጨማሪ ግን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ እንደታየው የሁለቱ ቡድኖች የጨዋታ አቀራረብ መመሳሰልና በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኙ የአጥቂና የተከላካይ መስመሮች የሚያፋጥጥ መሆኑ ደግሞ ጨዋታው ይበልጥ ተጠባቂ ያደርገዋል።

ወልቂጤ ከተማዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። በኢትዮጵያ መድን በኩል ግን ንጋቱ ገ/ስላሴ አሁንም በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን አብዲሳ ጀማል በቅጣት ምክንያት ነገ የመጨረሻ ጨዋታው ያመልጠዋል።

በሊጉ ሦስት ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በእኩሌታ አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ በመጀመርያው ዙር ደግሞ ባዶ ለባዶ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱም ቡድኖች የእርሰ በርስ ግንኙነት ወልቂጤ ከተማ ሦስት ግቦች ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ሁለት ግቦች አስቆጥሯል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ሀድያ ሆሳዕና

የጣና ሞገዶቹ ግስጋሴያቸው ለማስቀጠል ነብሮቹ ደግሞ ከሽንፈት ቶሎ ለማገገም የሚያካሂዱትን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች

ባስመዘገቧቸው ተከታታይ ነጥቦች ሽቅብ መውጣታቸው የቀጠሉት ባህርዳር ከተማዎች አንድ ጨዋታ እየቀራቸው ነጥባቸው ሰላሣ ሦስት አድርሰዋል። ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አራት ድልና ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች ተላቆ ወደ ድል መንገድ መመለሱ ደረጃውን እንዲያሻሽል ረድቶታል። በሊጉ በጉልህ የሚጠቀስ መሻሻል ካሳዩት ውስጥ የሚጠቀሰው ቡድኑ ከተከታታይ ድሎቹ በተጨማሪ የገጠማቸው ቡድኖች ጥንካሬ ማየትም ተገቢ ነው። በተጠቀሱት መርሀ ግብሮች መቻልና ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፎ በመጨረሻው ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ተለያይቷል። ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች የመለሰውና ብትልቅ ተጋድሎ የተገኘው የወላይታ ድቻው ድልም ሳይረሳ። በከባድ መርሀ ግብሮች የሰበሰባቸው ነጥቦች ብዛትም ቡድኑ ምን ያህል እንደተሻሻለ ያሳያሉ።

የጣና ሞገዶቹ ምንም እንኳ ውስን የግብ ማስቆጠር ክፍተት ቢታይባቸውም ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ የማይነቃነቅ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ገንብተዋል። በነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣትም በተመሳሳይ ጠንካራ የኋላ ክፍል ያለው ቡድን የሚፈትን የማጥቃት አጨዋወት ማበጀት ይኖርባቸዋል።

ከአስራ ስምንት ሽንፈት አልባ ሳምንታት በኋላ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ያስተናገዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከሽንፈቱ ቶሎ ለማገገድ የጣና ሞገዶቹን ይገጥማሉ። በመጨረሻው ጨዋታ በውድድር ዓመቱ ለሦስተኛ ጊዜ ከአንድ ግብ በላይ ያስተናገዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች በጨዋታው የኋላ ክፍላቸው ተፈትኗል።

ቡድኑ ምንም እንኳ መልካም አጀማመር አድርጎ ጨዋታውን መምራት ቢጀምርም የኋላ ኋላ ተዳክሞ ብልጫ ተወስዶበታል። በተለይም በሲዳማ የማጥቃት አጨዋወት የተፈተነው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ለተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲጋለጥ ነበር። ሀድያዎች ከሽንፈቱ በፊት በተከታታይ አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው ጠጣሩ የመከላከል አደረጃጀት መመለስ ዋነኛ ተግባራቸው እንደሚሆን ይጠበቃል። ከዚ በተጨማሪ በመጨረሻው ጨዋታ ካሳየው መጠነኛ መቀዛቀዝ ውጭ በአንፃራዊነት ጥሩ መሻሻሎች ያሳየው በዳዋ ሆቴሳና ተመስገን ብርሀኑ የሚመራው የቡድኑ የፊት መስመር የሞገዱ ጠንካራ የኋላ ክፍል ለመፈተን ብቁ መሆን ይኖርበታል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ሰባት ጊዜ ሲገናኙ ሀድያ ሆሳዕና አራት፤ የጣና ሞገዶቹ ደግሞ ሦስት ጊዜ አሸንፈዋል። በግንኙነቱ እኩል የግብ መጠን ያላቸው ሁለቱ ቡድኖቹ በሰባቱ ጨዋታዎች አምስት ግቦች በእኩሌታ አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)

ባህር ዳር ከተማዎች በቅጣት ምክንያት የሀብታሙ ታደሰና ያብስራ ተስፋዬ ግልጋሎት አያገኙም። ሀድያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው ጉዳት ላይ ያለው መለሰ ሚሻሞን አያሰልፉም።