መረጃዎች | 89ኛ የጨዋታ ቀን

የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ የሆኑትን ሁለት መርሀ ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

ኢትዮጵያ ቡና ከ መቻል

በጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከመቻል ያገናኛል።

አዳማ ከተማን በገጠሙበት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ ከአሰልጣኝ ለውጡ በኋላ ሦስተኛ ሽንፈታቸው ያስተናገዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በነገው ጨዋታ ድል ማድረግ ቢያንስ የአንድ ደረጃ እድገት ያስገኝላቸዋል።

ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ድል፣ አንድ አቻና ሦስት ሽንፈቶች ያስተናገደው ቡድኑ በውጤትም ይሁን በእንቅስቃሴ ረገድ ተከታታይነት ከነበረው ጥሩ ብቃት መንገራገጭ ከጀመረ ሰንበትበት ብለዋል። ቡድኑ ምንም እንኳን ሽንፈት ባስተናገደበት የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ባያደርግም አሸንፎ ደረጃውን ማሻሻል ግን አልተቻለውም።

ከመሪው በአስር ነጥቦች ርቀው የተቀመጡት ቡናማዎቹ በነገው ዕለት ከመቻል ጋር የሚያካሂዱት ጨዋታ ጨምሮ ቀጣይ ሁለት መርሃግብሮች ሙሉ ሶስት ነጥብ ካሳኩ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የሚጠጉበት ዕድል የሰፋ ነው። ይህ እንዲሆን ግን ቡድናቸው በሁሉም ረገድ ብቁ ማድረግ ግድ ይላቸዋል። በተለይም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ለተጠባቂ ጨዋታዎቹ የሚመጥን ጥንካሬ ተላብሶ መቅረብ ይገባዋል።

በተከታታይ ነጥብ የጣለው መቻል ከመሪው ያለው የነጥብ ልዩነት ለማጥበብም ሆነ ባለበት ለማስቀጠል ከዚህ መርሃግብር ሙሉ ነጥብ ማግኘት ይኖርበታል።

በመጨረሻው ጨዋታቸው በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ከተጋጣሚው ተመጣጣኝ ድርሻ የነበረው ቡድኑ የኋላ መስመር ለማስከፈት የጣረበት መንገድ መልካም ቢሆንም በሁለቱም አጋማሾች ያልተጠቀመባቸው ዕድሎች ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ እንዳይወጣ አድርጎታል። በነገው ጨዋታም ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ግቦች ያስተናገደው ጠንካራው የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ ከማስቀጠል አልፈው የአፈፃፀም ክፍተታቸው አርመው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በመቻል በኩልም የግራ መስመር ተከላካዩ ዳዊት ማሞ ቅጣቱን ጨርሶ ዝግጁ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 33 ጨዋታዎችን አድርገው ኢትዮጵያ ቡና 17 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 7 ጊዜ ድል አድርጎ በ9 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ቡናማዎቹ 52 ጦሩ ደግሞ 33 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሲዳማ ቡና

የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ በሆነው መርሃግብር መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲዳማ ቡናን ይገጥማል።

በሦስት ነጥቦች ልዩነት ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ንግድ ባንኮች መሪነታቸውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ንግድ ባንኮች ከሦስት ጨዋታዎች ነጥብ መጣል በኋላ ሁለት ተከታታይ ድሎች ማስመዝገባቸውና ተከታዮቻቸው ነጥብ መጣላቸው ተከትሎ በሊጉ አናት እንዲቀመጡ ሆኗል። ቡድኑ ከውጤት ባሻገር የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውም ጥሩ መሻሻል አሳይቷል ሆኖም በነገው ዕለት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጥሩ መሻሻሎች ያሳየና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት ያላስተናገደ ቡድን ስለሚገጥም የሚጠብቀው ፈተና ቀላል አይሆንም። ከዚህ በተጨማሪ የተከታዮቹን ውጤት አይቶ እንደመግባቱ ከሚገጥመውን ጫና ነፃ ሆኖ ለመጫወት ከወዲሁ በአእምሮ ረገድ መዘጋጀት ይኖርበታል።

አምስት ሽንፈት አልባ ሳምንታት አሳልፈው ደረጃቸውን ያሻሻሉት ሲዳማ ቡናዎች ከሰባት ሳምንታት በፊት ንግድ ባንክ ላይ ያሳኩት ድል መድገም ከቻሉ ሁለት ደረጃዎች መመንደግ ይችላሉ።

ሀድያ ሆሳዕናን ባሸነፉበት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ከወትሮው በተለየ ብልጫ ተጭነው የተጫወቱት ሲዳማ ቡናዎች ጠንካራው የሀድያ የመከላከል አደረጃጀት የሰበሩበት መንገድ በጨዋታው ድል አድርገው እንዲወጡ ረድቷቸዋል። በተለይም ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን ያላስደፈረው የተከላካይ ክፍልና ባለፉት መርሃግብሮች ጨዋታውን በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ ድርሻ የነበረው የአማካይ ክፍል የሚኖራቸው ዕለታዊ ብቃት የቡድኑ ውጤት ይወስናል ተብሎ ይገመታል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 17 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን አመዛኙ 10 ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነው። ሲዳማ 5 ጨዋታ ሲያሸንፍ ንግድ ባንክ ደግሞ 2 አሸንፏል። በግንኙነታቸው ሁለቱም ቡድኖች በእኩሌታ 20 ግቦች አስቆጥረዋል።